በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ወደ ታዳሽ የኃይል አማራጮች እየዞረ ይገኛል። በዚህ ረገድ የሰሜን አውሮፓዊቷ ሀገር ኖርዌይ፣ በተለይም መዲናዋ ኦስሎ፣ ለቀሪው ዓለም በተግባር የተረጋገጠ ታላቅ ትምህርት እየሰጡ ነው። ኖርዌይ አሮጌውን የነዳጅ መኪና ቴክኖሎጂ በኤሌክትሪክ መኪናዎች በመተካት ረገድ የደረሰችበት ደረጃ፣ ተአምራዊ በሚባል ፍጥነት እየተጓዘ ይገኛል።
ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በሀገሪቱ ከተሸጡት አዳዲስ መኪኖች መካከል 90 በመቶ ያህሉ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ (EVs) መሆናቸው ተመዝግቧል። ይህ ቁጥር ኖርዌይን በዘርፉ የዓለም ቁንጮ ያደርጋታል። በአንጻሩ በታላላቅ ሀገራት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም 20 በመቶ፣ በአሜሪካ ደግሞ 8 በመቶ ብቻ መሆኑ የኖርዌይን ስኬት ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ ያሳያል።
የዚህ ለውጥ ትልቁ ማሳያ በኦስሎ የሚገኘው ‘ሀራልድ ኤ ሞለር’ የተባለው አንጋፋ የመኪና አከፋፋይ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ለ75 ዓመታት የፎልክስዋገን የነዳጅ መኪናዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ሲያስገባ ቢቆይም፣ ከ2024 መጀመሪያ ጀምሮ ግን በነዳጅ የሚሠሩ መኪናዎችን መሸጥ አቁሟል። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኡልፍ ቶሬ ሄክነቢ እንደተናገሩት፣ "የወደፊቱ ጉዞ በኤሌክትሪክ መሆኑ ግልጽ በሆነበት ሁኔታ፣ ዛሬ ወደ እኛ የሚመጣን ደንበኛ የነዳጅ መኪና እንዲገዛ መምከር ስህተት ነው" በማለት ገበያው ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ያረጋግጣሉ።
በኦስሎ ጎዳናዎች ላይ የሚታየው ትዕይንትም ይህንኑ እውነት ያጠናክራል። በከተማዋ ከሚንቀሳቀሱ መኪኖች መካከል በታርጋቸው ላይ "E" የሚል ምልክት ያላቸው መኪኖች በብዛት ይታያሉ። ይህም መኪናው በኤሌክትሪክ የሚሠራ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ካሉ መኪኖች ሁሉ አንድ ሦስተኛ ያህሉ የኤሌክትሪክ መኪኖች ናቸው።
ይህ ውጤት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን፣ ለሦስት አሥርታት የታቀደ ሥራ ውጤት ነው። የኖርዌይ ኤሌክትሪክ መኪና ማኅበር ዋና ጸሐፊ ክሪስቲና ቡ እንደሚሉት፣ ሂደቱ የጀመረው በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ነው። መንግሥት የነዳጅ መኪናዎችን በቀጥታ ከመከልከል ይልቅ ሕዝቡ በራሱ ፍላጎት ወደ ኤሌክትሪክ እንዲዞር የሚያደርጉ ብልህ ፖሊሲዎችን ቀርጿል።
ዋነኞቹ ስልቶችም በነዳጅ መኪኖች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣል እና ለኤሌክትሪክ መኪና ገዢዎች ደግሞ ከተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እና ከገቢ ዕቃ ቀረጥ ነፃ የማድረግ ዕድል መስጠት ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የኤሌክትሪክ መኪና አሽከርካሪዎች ነፃ የመኪና ማቆሚያ፣ በአውቶቡስ መስመሮች የመጓዝ መብት እና በክፍያ መንገዶች ላይ ከፍተኛ ቅናሽ ያገኛሉ።
ኖርዌይ በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ከ27,000 በላይ የሕዝብ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ገንብታለች። ይህ በሕዝብ ብዛት ሲሰላ፣ ለእያንዳንዱ 100,000 ሰው 447 መሙያ ጣቢያዎች መኖራቸውን ያሳያል። ሀገሪቱ ያላት ግዙፍ የነዳጅ እና የጋዝ ሀብት ለኢኮኖሚዋ መሠረት ቢሆንም፣ ይህንኑ ሀብት በመጠቀም ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጋር የሚስማማ መሠረተ ልማት መገንባት መቻሏ ለሌሎች ሀገራት ትልቅ ልምድ ነው።
የሚገርመው ደግሞ ሀገሪቱ ለኤሌክትሪክ መኪኖቿ የምትጠቀመው ኃይል 88 በመቶው ከታዳሽ የውኃ ኃይል የሚመነጭ መሆኑ ነው። ኖርዌይ በ2025 በሀገሪቱ የሚሸጡ አዳዲስ መኪኖች በሙሉ "ዜሮ በካይ ጋዝ" እንዲሆኑ ግብ አስቀምጣ ስትሠራ ቆይታለች። ይህ ግብ አሁን ካለው ፍጥነት አንጻር በቀላሉ እንደሚሳካ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ዛሬ ላይ በኖርዌይ የናፍጣ መኪና መግዛት የሚፈልግ ሰው ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል።
የኖርዌይ ልምድ እንደሚያሳየው፤ ግልጽ የሆነ የመንግሥት ፖሊሲ፣ ወጥ የሆነ የታክስ ማበረታቻ እና የመሠረተ ልማት ዝግጅት ከተጣመረ፣ ዓለምን ከካርቦን ብክለት ማዳን የሚችል ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
በላሉ ኢታላ