Search

የኢራን ጦርነት ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ውስጥ ሊያበቃ ይችላል:- ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ረቡዕ መጋቢት 23, 2018 80

በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰውና የዓለምን ኢኮኖሚ እያናጋ የሚገኘው ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊቆም እንደሚችል የሚጠቁሙ አዳዲስ ተስፋ ሰጪ መረጃዎች ተሰምተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትላንት በሰጡት መግለጫ፣ አሜሪካ በኢራን ላይ የምታደርገውን ጥቃት ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ልታቆም እንደምትችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
 
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ጦርነቱን ለማቆም የግድ የሰላም ስምምነት መፈረም ላያስፈልግ እንደሚችል በመግለጽ ግጭቱ በቅርቡ ሊያበቃ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ አሜሪካ በጣም በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምናልባትም በሁለት ወይም በሦስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ከአካባቢው እንደምትወጣም ጠቁመዋል።
 
ኢራን ለረጅም ጊዜ ወደ ኒውክሌር መሣሪያ ማበልጸግ የማትችልበት ደረጃ ላይ መድረሷን ስናረጋግጥ አካባቢውን ለቀን እንወጣለን ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ይህ የትራምፕ መግለጫ የተሰማው በአሜሪካ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ተከትሎ በፕሬዝዳንቱ ላይ የሚሰነዘረው የውስጥ ግፊት በበረታበት ወቅት ነው ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።
 
ምንም እንኳን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ከአሜሪካ ጋር ቀጥተኛ ድርድር እየተደረገ አለመሆኑን ቢገልጹም በሁለቱ ሀገራት መካከል በተዘዋዋሪ የሚደረጉ የመልዕክት ልውውጦች ግን ለሰላም ጥረቱ በር ከፋች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ኢራን የኒውክሌር እንቅስቃሴዋ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ እንደሆነና የኒውክሌር መሣሪያ ለማምረት ፈልጋ እንደማታውቅ በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ ይታወሳል።

በጌቱ ላቀው