ዓለማችን በአሁኑ ወቅት የኃይል ሚዛን ሽግግር የሚታይበትና ባለብዙ ዋልታ ሥርዓት እየተቀረጸበት በሚገኝ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።
ይህ ወቅታዊ ለውጥ ካለፉት የታሪክ አጋጣሚዎች በተለየ መልኩ፣ ያለምንም ታላቅ ዓለም አቀፍ ግጭት በሂደት እየተከወነ የሚገኝ መዋቅራዊ ሽግግር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።

በዚህ የሽግግር ወቅት የ"ግሎባል ሳውዝ" ሀገራት ያላቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተጽዕኖ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የተለያየ ባህላዊና መልክዓ-ምድራዊ ስብጥር ያለው አዲስ አሰላለፍ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥም የብሪክስ ሀገራት ያላቸው የኢኮኖሚ ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱ፣ የዓለም የንግድና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች በባለብዙ አማራጭ የክፍያ ሥርዓቶች ላይ እንዲመሰረቱ ፍላጎቶች እንዲጎለብቱ አድርጓል።

አሁን ላይ ሀገራት የራሳቸውን የሀገር ውስጥ ገንዘቦችና ሌሎች አማራጭ የፋይናንስ መሣሪያዎችን በስፋት መጠቀም እንዲጀምሩ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ይገኛል።
ይህ ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ ያለውን ጥገኝነት ወደ ሚዛናዊና ሁሉን አቀፍ አማራጭነት የመቀየር ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተደርጎ ይወሰዳል።
ወደፊት የሚታዩት ለውጦች በዋናነት በኃያላን ሀገራት መካከል ባለው የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ፉክክር፣ እንዲሁም ታዳጊ ሀገራት በዓለም አቀፍ መድረክ የራሳቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ አማራጮች ለማጠናከር ባላቸው ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረቱ ናቸው።

የዓለም የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ሽግግር የማይቀለበስና ሁሉንም ወገኖች ያካተተ ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን በዘርፉ ያሉ ምሁራን ይተነትናሉ።
ይህ አዲስ የዓለም ሥርዓት በጋራ ተጠቃሚነትና በዲፕሎማሲያዊ መግባባት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሁሉም ሀገራት ሚና ወሳኝ ሆኖ ይቀጥላል።
በሰለሞን ገዳ