ዓለም ትንፋሿን ውጣ በከፍተኛ ስጋት የምትመለከተው የካቲት 21 የተቀሰቀሰው የአሜሪካ/እስራኤል እና የኢራን ጦርነት፣ ዛሬ 35ኛ ቀኑን ይዟል።
ይህ በአንድ ቀጣና ተወስኖ የቀረ የሚመስል ፍጥጫ፣ ባልታሰበ ፍጥነት አድማሱን አስፍቶ የዓለምን ኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እና የሰው ልጅ ደኅንነት ማነቆ ሆኗል።
ከኢራን ሰማይ ላይ ከሚዘንቡት ሚሳኤሎች ተመትተው እስከሚወድቁ ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች፤ በባህረ ሰላጤው ላይ የሚደርሰው የሚሳኤል ውርጅብኝ፤ ከናረው የነዳጅ ዋጋ እስከ ተቋረጡ ዓለም አቀፍ በረራዎች ድረስ ያለው የ35 ቀናት የጥፋት ጉዞ፣ ዓለማችንን ወደ ማይታወቅ አደገኛ ምዕራፍ እየመራት ይገኛል።
መላው ዓለም በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በገለልተኝነት እየተከታተለው ያለውን የዚህን አውዳሚ ግጭት የ35 ቀናት ሂደት እና ዓለም አቀፍ አንድምታዎቹን እንደሚከተለው በዝርዝር እንቃኛለን።

ማንኛውም ጦርነት መነሻውም ሆነ መድረሻው ምንም ይሁን ምን፣ የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች ንጹሐን ዜጎች ናቸው። በኢራን እና አሜሪካ/እስራኤል ጦርነትም የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ይህንኑ አረጋግጠዋል።
ይህ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ከመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል።
ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 2 ሺህ 76 ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 26 ሺህ 500 የሚሆኑት ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ይህ አኃዝ የጦርነቱን አስከፊነት ከማሳየቱም በላይ፣ ጥቃቶቹ ወታደራዊ ይዘት ያላቸውን ስፍራዎች ብቻ ሳይሆን ንጹሐን የሚኖሩባቸውን አካባቢዎችም እያዳረሱ መሆኑን አመላካች ነው።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ600 በላይ ትምህርት ቤቶች እና የትምህርት ማዕከላት መመታታቸውን ገልጿል።
ጦርነቱ ወደ ሦስተኛው ሳምንት ሲሸጋገር፣ ግጭቱ በሁለቱ ዋና ተፋላሚዎች መካከል ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ኢራን ጥቃቷን በማስፋት ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራት አሸጋግራለች።
ይህም በኩዌት እና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ላይ በተሰነዘሩት ጥቃቶች በግልጽ የታየ ሲሆን፣ የኩዌት የኃይል ማመንጫ እና የውኃ ማጣሪያ ፋብሪካዎች መመታታቸው ጦርነቱ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ዒላማ ማድረጉን አጋልጧል።
በተለይም የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በአንድ ቀን ብቻ 18 ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን እና 47 ድሮኖችን ማክሸፏ፣ የቀጣናው ሀገራት ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ በከፍተኛ ወታደራዊ ዝግጁነት እንደሚገኙ ያሳያል።
የዚህ ጦርነት ተፅዕኖ ከባህረ ሰላጤው አልፎ ዓለም አቀፉን ገበያ እያናጋው ይገኛል። የዓለማችን 20 በመቶ ነዳጅ የሚያልፍበት የሆርሙዝ ሰርጥ ደኅንነት አደጋ ላይ መውደቁ፣ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን አስተጓጉሏል።
በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት በማሻቀብ፣ የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በላይ ሆኖ ተመዝግቧል። የሩሲያው 'ኡራልስ' (Urals) ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 123.45 ዶላር ሲያድግ፣ የብሬንት (Brent) ዋጋ ደግሞ ከ109 ዶላር በላይ ሆኗል። ይህ የዋጋ ንረት በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ጫና ከመፍጠሩም በላይ፣ የኑሮ ውድነትን በከፍተኛ ደረጃ እያባባሰ ይገኛል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፉ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ከባድ የኢኮኖሚ ምት እየደረሰበት ነው። ዘርፉ ለ2026 ዓ.ም የ41 ቢሊዮን ዶላር የትርፍ ግብ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ ምክንያት ይህ ዕቅድ ትልቅ ፈተና ገጥሞታል።
በዚህም ሳቢያ እንደ ኤር ኒው ዚላንድ እና ቪየትናም አየር መንገድ ያሉ ኩባንያዎች የበረራ ቁጥራቸውን ለመቀነስ የተገደዱ ሲሆን፣ ኮሪያን ኤርን የመሳሰሉ ግዙፍ ተቋማት ደግሞ የገጠማቸውን ኪሳራ ለመቋቋም አስተዳዳራዊ እርምጃዎችን ወደ መውሰድ ተሸጋግረዋል።
በአራተኛው እና አምስተኛው ሳምንታት፣ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት የሚደረጉ ጥረቶች ሲስተጓጎሉ ተስተውሏል። አሜሪካ ያቀረበችው የ48 ሰዓት የተኩስ አቁም ጥያቄ በኢራን በኩል ውድቅ መደረጉ፣ እንዲሁም የኢራን ጦር "ጠላቶቻችን እጅ እስኪሰጡ እንዋጋለን" የሚል ጠንካራ አቋም ማንጸባረቁ የዲፕሎማሲውን በር አጥብቦታል።
በአሜሪካ በኩልም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን ቅድመ ሁኔታዎችን ካልተቀበለች አገሪቱን ወደ "ድንጋይ ዘመን" እንደሚመልሷት ማስጠንቀቃቸው፣ ውጥረቱን ይበልጥ አባብሶታል።
ይህ በንዲህ እንዳለ ምክንያቱ ምን አንደሆነ ባይገለፅም የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር የጦር ሠራዊቱን ዋና ጄኔራል እና ሌሎች ከፍተኛ መኮንኖችን በጦርነት መሐል ከሥራ ማሰናበታቸው መነጋገሪያ ሆኗል።
በሌላ በኩል አሜሪካ ባልተሳተፈችበት መድረክ፣ ብሪታንያ የሆርሙዝን የባህር ሰርጥ ደኅንነት ለማስጠበቅ ከ40 ሀገራት ጋር የጀመረችው ውይይት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የራሱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አማራጭ የዲፕሎማሲ መንገዶችን እየፈለገ መሆኑን ያሳያል።
የ35 ቀናቱ የክስተቶች ሂደት እንደሚያሳየው፣ ወታደራዊው ፍጥጫ ይበልጥ ውስብስብ እየሆነ መጥቷል። የአሜሪካ አየር ኃይል ንብረት የሆኑት F-15E Strike Eagle እና A-10 Warthog ተዋጊ ጄቶች በኢራን ሰማይ ላይ ተመትተው መውደቃቸው የኢራንን የአየር መከላከያ አቅም ያሳየ ሆኗል።

የወደቁትን አብራሪዎች ለመፈለግ የተሰማሩ የነፍስ አድን ሄሊኮፕተሮች ላይ ጥቃት መድረሱ ደግሞ፣ ተልዕኮዎቹ ምን ያህል አደገኛ እና ጊዜን የሚሻሙ መሆናቸውን ያረጋግጣል። የነፍስ አድን ቡድኖች አንዱን አብራሪ ማዳን ቢችሉም፣ ሁለተኛውን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት ጦርነቱ እጅግ ፈታኝ ወታደራዊ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ማሳያ ነው።
ይህ የ35 ቀናት የጦርነት ቆይታ የሚያሳየው፣ ግጭቱ ከወታደራዊ ፍጥጫነት አልፎ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የትራንስፖርት እና የዲፕሎማሲ ቀውስ መፍጠሩን ነው። ሁሉም ወገኖች ከጥቃት እና አጸፋዊ ጥቃት አዙሪት ወጥተው ወደ ድርድር ጠረጴዛ ካልመጡ፣ ጦርነቱ በቀጣናው ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ላይ የሚያስከትለው ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ስብራት በቀላሉ የማይጠገን ይሆናል። ይህን አውዳሚ ጦርነት በማስቆም ረገድ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሚዛናዊ እና ተጨባጭ የሰላም ጥረቶችን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
#world #middleeast #iran #usa #israel