Search

ጉግል ምድርን በጥራት ማየት የሚያስችል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴል አስተዋወቀ

Aug 11, 2025

ጉግል የዓለምን እያንዳንዱ ስፍራ የአየር ላይ ምስል ግልፅ በሆነ መንገድ የሚያሳይ “አልፋ ኧርዝ ፋውንዴሸን” የተባለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሞዴል አስተዋውቋል።

አዲሱ ቴክኖሎጂ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ ከዋሉት የአየር ላይ ምስል አቅራቢዎች የተሻለ ጥራት እንዳለውም ተገልጿል።

አዲሱ ሞዴል ምድርን በሚዞሩ ሳተላይቶች ላይ ብቻ ከመመርኮዝ  ይልቅ መረጃዎችን ከሶስት ዲያሜንሽን (3D) ካርታዎች፣ ከሳተላይት ምስሎች እና ከራዳር ጋር በማጣመር ዝርዝር እና ወቅታዊ ካርታዎች ለመፍጠር ይጠቅማል ተብሏል።

ይህም በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ምስሎችን አጣምሮ ዝርዝር መረጃዎችን በመፍጠር ሳይንቲስቶች የምድርን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በንቃት እንዲከታተሉ ይረዳል ሲል ኢሮ ኒውስ ዘግቧል።

እ.አ.አ. ከ2017 እስከ 2024 ያለውን መረጃ በመጠቀም በተደረገው የመጀመሪያ ሙከራ፣  አልፋ ኧርዝ ፋውንዴሸን ሌሎች  የዲጂታል ካርታ ሞዴሎችን የሚሰሩትን ስህተት 24 በመቶ መቀነስ መቻሉን ጎግል አስታውቋል።

እንዲሁም "ከአልፋ ኧርዝ ፋውንዴሽን" የተገኘው መረጃ ከተመሳሳይ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ስርዓቶች በጣም ያነሰ የማከማቻ ቦታን የሚጠይቅ ሲሆን ይህም መጠነ ሰፊ ትንታኔን የበለጠ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል ብሏል ኩባንያው።

ጎግል አዲስ ያስተዋወቀው ሞዴል ተመራማሪዎች የምግብ ዋስትና ሥራዎችን፣ የደን ጭፍጨፋን፣ የከተማ መስፋፋትን እና የውሃ ሀብት ለውጦችን እንዲያጠኑ ይረዳቸው ሲል ዘገባው አመላክቷል።

 

 

በሴራን ታደሰ

 #EBC #ebcdotstream #google #map #Artificialinteligence