የመንገድ መሠረተ ልማት ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት ያለው ፋይዳ የሚሰጥ ወሳኝ እና የማይተካ የጀርባ አጥንት ነው።
መንገዶች የንግድ ትሥሥርን በማሳለጥ፣ የትራንስፖርት ወጪን በመቀነስ እና ዜጎችን ከማኅበራዊ አገልግሎቶች ጋር በማገናኘት ረገድ የሚጫወቱት ሚና ለዘላቂ ብልጽግና መሠረት ይሆናል።
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ወዲህ የታየው ሁለንተናዊ ለውጥም ይህንን እውነት መነሻ በማድረግ፤ በመንገድ መሠረተ ልማት ዘርፍ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስልታዊ ሽግግር ሆኖ ተመዝግቧል።
እስከ 2009 ዓ.ም ባለው ጊዜ የኢትዮጵያ የመንገድ መሠረተ ልማት በአምስተኛው የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም (RSDP V) ሥር መጠነ ሰፊ ግንባታዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
በወቅቱ ማብቂያ ላይ የሀገራችን አጠቃላይ የመንገድ አውታረ መረብ ርዝመት 121 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር ደርሶ ነበር።
በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የነበረው ርዝመት 5 ሺህ 915 ኪሎ ሜትር እንደነበረ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

የፈጣን የክፍያ መንገዶችን በተመለከተም በጊዜው አገልግሎት ላይ የነበረው ብቸኛ ፈጣን መንገድ 80 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ - አዳማ መንገድ ብቻ ነበር።
ባለፉት ስምንት ዓመታት መንግሥት የመንገድ ዘርፉን የሀገራችን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ዋና ምሰሶ በማድረግ፣ ከመደበኛ ግንባታ ባለፈ ወደ ስልታዊ የሀብት አስተዳደር የተሸጋገረበትን አዲስ የፖሊሲ አቅጣጫ ተግባራዊ አድርጓል።
ከ2010 ዓ.ም በኋላ ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ የመንገድ መሠረተ ልማት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ አዲስ የታሪክ አሻራ አኑሯል።
ነሐሴ 2017 ዓ.ም የወጣው የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የሀገራችን የመንገድ አውታረ መረብ ርዝመት ከ180 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ደርሷል።

ይህ ዕድገት ኢትዮጵያን በመንገድ አውታረ መረብ ርዝመት ከአፍሪካ ቀዳሚዎቹ ሀገራት ተርታ አሰልፏታል።
ያለፈው ዓመት የዓለም ባንክ ሪፖርት እንሚያመለክተው የሀገራችን የመንገድ ጥግግት በ1 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር 148.3 ኪሎ ሜትር ደርሷል።
ይህ የተሻለ የመንገድ ትሥሥር ባለባቸው አካባቢዎች የግብርና ምርታማነት በ14.7 በመቶ እንዲያድግ እና የዜጎች እውነተኛ ገቢ በ22 በመቶ እንዲጨምር ማድረጉን የዓለም ባንክ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ ታላቅ የልዩነት ለውጥ የመጣው መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና በፖሊሲ ለውጦች ምክንያት ነው።
የመንገድ ግንባታ በየዓመቱ ከሀገራዊ የካፒታል ወጪ ከ30 በመቶ በላይ ድርሻ የሚይዝ ነው።
ለምሳሌ በ2017 በጀት አመት 94.4 ቢሊዮን ብር እንዲሁም በ2018 በጀት ዓመት ደግሞ 89.1 ቢሊዮን ብር መመደቡን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በተጨማሪም ግንባታው ከሀብት ግንባታ ወደ ሀብት አስተዳደር እንዲሸጋገር መደረጉ፣ 79 በመቶ የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በሀገር በቀል ተቋራጮች እንዲከናወኑ መበረታታቸው እና የአፈጻጸም ምዘና ሥርዓት መዘርጋቱ ለውጡ እንዲፋጠን ረድተዋል።
የፈጣን መንገዶች ማስፋፊያም ቢሆን ከ2010 ዓ.ም በኋላ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። እስከ 2009 ዓ.ም ከነበረበት 80 ኪሎ ሜትር ተነስቶ በ2018 ዓ.ም ወደ 301 ኪሎ ሜትር ማደጉን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም መካከል የሞጆ-ሀዋሳ የፈጣን መንገድ ግንባታ በዋነኝነት የሚጠቀስ ሲሆን፣ የሞጆ-መቂ እና መቂ-ዝዋይ ክፍሎች ተጠናቅቀው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት የዝዋይ-አርሲ ነገሌ ክፍል ግንባታ 93.7 በመቶ አፈጻጸም ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቅርቡ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ሌሎች ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶችንም በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል። በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን 1.3 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት 75.6 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
ከዚህ በተጨማሪ የነቀምት - ቡሬ የሎት 2 መንገድ ግንባታ 98.5 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ የአዋሽ-ቁሉቢ-ድሬዳዋ/ሐረር የአስፋልት እድሳት ሥራዎችም ከ80 በመቶ በላይ አፈጻጸም ላይ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ ከተማም የመንገድ መሠረተ ልማቱ ከ2010 ዓ.ም በኋላ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
የከተማዋ አጠቃላይ የመንገድ ርዝመት በ2018 ዓ.ም 6 ሺህ 573 ኪሎ ሜትር ደርሷል። በተለይም ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የከተማዋን ገጽታ የቀየረ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ 40 ኪሎ ሜትር እና ሁለተኛው ምዕራፍ 132 ኪሎ ሜትር በድምሩ 172 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ኮሪደሮችን ያካትታል።
ይህ ፕሮጀክት በከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅን በ30 በመቶ እንደሚቀንስ የሚገመት ሲሆን፣ ለዜጎችም 96 ኪሎ ሜትር የእግረኛ እና 100 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገዶችን አበርክቷል።
ይህ የተሳካ ተሞክሮ በአሁኑ ወቅት ወደ ሌሎች 75 የሀገራችን ከተሞች እየተስፋፋ ይገኛል። ለምሳሌ በባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች 32.23 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ እና 25 ኪሎ ሜትር የመንገድ መብራት ሥራዎችን ያካተተ የኮሪደር ልማት ተጀምሯል።
እነዚህ ባለፉት ስምንት ዓመታት የተመዘገቡት ስኬቶች የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ተወዳዳሪነት ከማሳደጋቸውም ባለፈ፣ የገጠር ነዋሪዎችን ወደ አምራችነት በመለወጥ ለሀገራዊ ብልጽግና ጉዞ አስተማማኝ መሠረት ጥለዋል።
የመንገድ መሠረተ ልማት እመርታ ሀገራዊ የውስጥ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማሳለጥ ብቻ የተገደበ አይደለም፤ ይልቁንም ኢትዮጵያን የክፍለ አህጉሩ የኢኮኖሚና የንግድ ማዕከል እንድትሆን በማስቻል ለቀጣናዊ ትሥሥር የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
በተለይም ከጎረቤት ሀገራት ከሆኑት ኬንያ፣ ጂቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ጋር የተዘረጋው ጠንካራ የመንገድ ትሥሥር የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ የቀጣናውን የነገ ብልጽግና ተስፋ በተጨባጭ መሬት ላይ እያሳየ ነው።
በአጠቃላይ ይህ በሪፎርም የታጀበና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመሠረተ ልማት ሽግግር ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ትንሳኤ እጅግ ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ታሪካዊ ክስተት ነው።
በለሚ ታደሰ