Search

ኢራን እና አሜሪካ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማሙ

ረቡዕ መጋቢት 30, 2018 167

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ሲያወጁ፤ ኢራን በበኩሏ የሆርሙዝ ሰርጥን ለመክፈት ተስማማታለች።

ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል የሚደረገው አስተማማኝ ጉዞ በታጠቁ ኃይሎቿ አማካኝነት በሚደረግ ቅንጅት እንደሚከናወን ገልጻለች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ቴህራን ያቀረብኩትን ጥያቄ ካልተቀበለች "ዛሬ ምሽት አንድ ሙሉ ሥልጣኔ ይጠፋል" የሚል ዛቻ ሰንዝረው የነበረ ቢሆንም፣ በኢራን ላይ ሊያካሂዱት የነበረውን የቦምብ ጥቃት ለሁለት ሳምንታት ለማገድ ተስማምተዋል። 

ትራምፕ ጥቃቱ ሊፈጸም ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት "ትሩዝ ሶሻል" በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ውሳኔያቸውን መቀልበሳቸውን አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ስምምነት መሳካት ፓኪስታን ላደረገችው ሽምግልና እውቅና የሰጡ ቢሆንም፣ ስምምነቱ ግን ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን እንድትከፍት የሚል ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠበት መሆኑን አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ በመልዕክታቸው፡- "ከፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሸሪፍ እና ከፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ጋር ባደረግሁት ውይይት፣ እንዲሁም ዛሬ ምሽት ወደ ኢራን ሊላክ የነበረው አጥፊ ኃይል እንዲቆይ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፤ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የሆርሙዝ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ፣ በአፋጣኝ እና በአስተማማኝ ሁኔታ ለመክፈት ከተስማማች፣ በኢራን ላይ የታቀደውን ጥቃት ለሁለት ሳምንታት ለማገድ ተስማምቻለሁ" ሲሉ ጽፈዋል።

ይህ መልዕክት የተላለፈው ትራምፕ ጥቃቱን ለመፈጸም ካስቀመጡት የጊዜ ገደብ አንድ ሰዓት ከግማሽ ያነሰ ጊዜ ሲቀረው እንደነበር አልጀዚራ ዘግቧል።

የትራምፕን መልዕክት ተከትሎም የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ጊዜያዊ ስምምነት ላይ መደረሱን አረጋግጠዋል።

"በኢራን ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች የሚቆሙ ከሆነ፣ የእኛ ብርቱ የታጠቁ ኃይሎች የመከላከል እርምጃቸውን ያቆማሉ" ሲሉ ነው አራቅቺ የገለጹት።

"ለሁለት ሳምንታት ያህል በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል የሚደረግ አስተማማኝ ጉዞ ከኢራን የታጠቁ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ቅንጅት እና ቴክኒካዊ ውስንነቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚቻል ይሆናል" ሲሉም አክለዋል።

አራቅቺም በተመሳሳይ ፓኪስታን የአሜሪካውን ጥቃት ለማስቆም ላደረገችው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢራን ከፍተኛ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት በሰጠው የተለየ መግለጫ፣ ድርድሩ በጥሩ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ የተኩስ አቁሙ መነሻ ከሆነው የሁለት ሳምንት ጊዜ በላይ ሊራዘም እንደሚችል ጠቁሟል።

ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸውን ድል አድራጊነት አብስረዋል።

እስራኤልም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰውን ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት በበጎ እንደምትመለከተው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መግለጻቸውን አር.ቲ ዘግቧል።

በዮናስ በድሉ

#EBC #world #middleeast #iran #usa #peace