Search

የአንድ በርሜል ድፍድፍ የነዳጅ ዋጋ በ13 በመቶ ቅናሽ አሳየ

ረቡዕ መጋቢት 30, 2018 86

ባለፉት አምስት ሳምንታት ዓለምን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ጥሎ የቆየውና ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር የነበረው የአሜሪካ እና የኢራን ግጭት ትላንት በተደረሰ የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ጊዜያዊ እፎይታን አግኝቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ሲቪል መሰረተ ልማቶች ለማውደም ያስቀመጡት የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰዓታት ሲቀሩት የታወጀው ስምምነቱ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ በጎ ተፅዕኖ ይዞ መጥቷል፡፡
የስምምነቱ መበሰር በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ ፈጣን ለውጥ ያመጣ ሲሆን፤ አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በ13 በመቶ ቅናሽ በማሳየት ወደ 91 ዶላር ዝቅ ማለቱን ሮይተርስ እና አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግበዋል፡፡
ይህ የዋጋ መቀነስ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ነዳጅ አስመጪ ሀገራት ትልቅ እፎይታ ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ የአክሲዮን ገበያዎችም በስምምነቱ ማግስት ከፍተኛ መነቃቃት አሳይተዋል፡፡
የዚህ ዲፕሎማሲያዊ ድል ቁልፍ ባለቤት ፓኪስታን ስትሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ እና የጦር ኃይሎች አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ለሳምንታት በምስጢር ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ለውጤት በቅቷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሻሪፍ ስምምነቱን "ጥበባዊ እርምጃ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ ለቀጣይ የሰላም ውይይት ሁለቱንም ሀገራት ወደ እስላማባድ ጋብዘዋል፡፡
ከፓኪስታን በተጨማሪ ኦማን የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥን በቴክኒክ ለማስተዳደር መስማማቷ እና ቻይና በኢራን ላይ ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ግፊት ለስምምነቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ናቸው፡፡
እንደ ግሎባል ታይምስ ዘገባ ከሆነ፤ ቻይና እና ሩሲያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል ሚዛኑን የጠበቀ ግፊት ማድረጋቸው ዋሽንግተን እና ቴህራን ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡ ረድቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን ስምምነት "ለዓለም ሰላም ትልቅ ቀን" ሲሉ የገለጹት ሲሆን፤ ስምምነቱ መካከለኛው ምሥራቅ ወደ "ወርቃማው ዘመን" እንዲሸጋገር በር ይከፍታል የሚል እምነት አላቸው፡፡
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በበኩላቸው፤ የሆርሙዝ ሰርጥ ለሁለት ሳምንታት ክፍት ሆኖ መርከቦች በሰላም እንዲያልፉ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው፤ ስምምነቱን እንደሚደግፉ ገልጸው፤ ሆኖም ይህ ተኩስ አቁም በሊባኖስ በኩል ያለውን ውጊያ እንደማይጨምር በማሳሰቢያነት ገልጸዋል፡፡
ኔታንያሁ አሜሪካ በድርድሩ ወቅት የእስራኤል የደኅንነት ስጋቶች ማለትም የኢራን ኑክሌር እና ሚሳይል ፕሮግራም እንዲገታ እንደምትሠራ ቃል እንደገባችላቸው ለሲ.ቢ.ኤስ ተናግረዋል ፡፡
ዓለም አቀፍ ተንታኞች ስምምነቱን ጥንቃቄ በተሞላበት ተስፋ እያዩት ይገኛሉ፡፡ የላንዡ ዩኒቨርሲቲው ተንታኝ ዡ ዮንግባኦ እንደሚሉት፤ ሁለቱም ሀገራት ጦርነቱ የሚያስከትለውን ሊሸከሙት የማይችሉትን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ኪሳራ በመገንዘባቸው ወደ ድርድር መጥተዋል፡፡
ኤም.ኤስ.ቲ ማርኪ የተባለው ተቋም ተንታኝ ሳውል ካቮኒክ ደግሞ፤ ስምምነቱ ለዓለም ነዳጅ ገበያ ጊዜያዊ መውጫ መንገድ እንደፈጠረ ገልጸው፤ ዘላቂ መረጋጋት የሚመጣው ግን በመጪው ዓርብ በእስላማባድ የሚጀመረው ድርድር ውጤታማ ሲሆን ብቻ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አልጀዚራ በዘገባው እንዳመለከተው ስምምነቱን ተከትሎ በቴህራን እና በዋሽንግተን ጎዳናዎች የታየው ደስታ ሕዝቡ ከጦርነት ስጋት መላቀቁን የሚያሳይ ትልቅ ምልክት ነው፡፡
የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም፤ የዓለምን የኢኮኖሚ ደም ስር የሆነውን የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ እንዲከፈት ማድረጉ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መታደጉ ትልቁ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት አሁን ያረፈው በእስላማባድ በሚደረገው ድርድር ላይ ሲሆን፤ ይህ ጊዜያዊ ስምምነት ወደ ዘላቂ የሰላም ስምምነት ተቀይሮ የዓለም ኢኮኖሚ እና ደኅንነት ይበልጥ እንዲረጋገጥ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
በለሚ ታደሰ