ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ኢራንን ለማጥፋት" የሰጡት የጊዜ ገደብ ሊያበቃ አንድ ሰዓት ተኩል ሲቀረው፣ አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በዚህም መሠረት ቴህራን የሆርሙዝ ሰርጥን ለጊዜው ለመክፈት ተስማምታለች። እስራኤልም በተኩስ አቁም ስምምነቱ መስማማቷን አስታውቃለች።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ጥቃቶችን የመሰንዘር ዕቅዳቸውን ማቆማቸውን ሲያስታውቁ፣ ከኢራን ለድርድር መሠረት ሊሆን የሚችል ባለ 10 ነጥብ የሰላም ሐሳብ እንደደረሳቸው ገልጸዋል።
በፓኪስታን አሸማጋይነት ለዋይት ሐውስ የቀረበው ዕቅድ፣ ቀደም ሲል አሜሪካ ውድቅ ያደረገቻቸውን ነጥቦች ያካተተ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦
መርከቦች በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል በሰላም እንዲያልፉ ኢራን የምትፈቅድ ቢሆንም፣ ጥበቃው ግን ወታደራዊ አመራሮቿ ሥር እንደሚሆን ገልጻለች።
በተጨማሪም ኢራን እና ኦማን በሰርጡ በሚያልፉ መርከቦች ላይ እስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ክፍያ እንዲያስከፍሉ እና ገንዘቡንም ለኢራን መልሶ ግንባታ እንዲውል ዕቅዱ ይፈቅዳል።
የሰላም ንግግሩ ካልተሳካ ግን ቴህራን ሰርጡን ዳግም ልትዘጋ እንደምትችል ተመልክቷል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ውሳኔውን ቢደግፉም፣ ስምምነቱ ግን ሊባኖስን እንደማያካትት ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ ስምምነቱ ሊባኖስንም ጭምር እንደሚጨምር ተናግረዋል።
ቻይናም ኢራን ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንድትመጣ ከፍተኛ ግፊት ማድረጓ ተገልጿል።
ቀጣዩ እርምጃ
አሸማጋዩ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሸህባዝ ሻሪፍ፣ የአሜሪካ እና የኢራን ልዑካን ቡድኖች በመጪው ዓርብ በኢስላማባድ እንዲገናኙ ጥሪ አቅርበዋል።
ዋይት ሐውስ ከኢራን ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር እያሰበ መሆኑን የገለጸ ቢሆንም እስካሁን የመጨረሻ ውሳኔ ላይ አልተደረሰም።
የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ እንዲረጋጋ እና በቀጣናው ያለውን ውጥረት ለጊዜውም ቢሆን ለማርገብ ትልቅ ተስፋ ሆኗል።
በመሐመድ ፊጣሞ