Search

ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ አስተዳደር ላይ እያሳየች ያለችው አፈጻጸም ደካማ ነው"፡- ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ዓርብ ሚያዝያ 02, 2018 133

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል የሚያልፈውን የነዳጅ ንግድ የምትመራበት መንገድ "በጣም ደካማ አፈጻጸም" የታየበት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ፕሬዚዳንቱ ‘ትሩዝ ሶሻል’ በተሰኘው የማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት "ይህ እኛ የተስማማንበት ስምምነት አይደለም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ኢራን የሁለት ሳምንቱን የተኩስ አቁም ስምምነት ውል ጥሳለች በማለት በዚህ ወሳኝ የንግድ መስመር ላይ በሚያልፉ መርከቦች ላይ ቀረጥ እንዳትጥልም አስጠንቅቀዋል።
ባለፈው ማክሰኞ የሁለት ሳምንቱ የተኩስ አቁም በታወጀበት ወቅት በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በሕንድ ውቅያኖስ መካከል የሚገኘው የሆርሙዝ ሰርጥ ዳግም ክፍት እንደሚሆን ኢራን እና አሜሪካ ገልጸው የነበረ ቢሆንም፤ የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ በሰርጡ በኩል ያለፉት 10 መርከቦች ብቻ መሆናቸውን የባሕር ትራንስፖርት መከታተያ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኢራን በመርከቦች ላይ ክፍያ መጠየቅ መጀመሯን ተከትሎ በቀጣናው ውጥረቱ እንደገና ያገረሸ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ "ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል በሚያልፉ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ የምታስከፍለውን ክፍያ አሁኑኑ ማቆም አለባት!" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ኢራን በሰርጡ በሚተላለፉ የንግድ መርከቦች ላይ በጦርነቱ ለወደሙ መሠረተ ልማት ሥራዎች ካሣ የሚውል ነው በሚል የክፍያ ሥርዓት መተግበር በመጀመሯ፣ የሰላም ስምምነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ተሰግቷል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ