Search

የመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ተስፋ እና ዓለም በትኩረት የሚጠባበቀው የድርድር ዋዜማ በኢስላማባድ

ዓርብ ሚያዝያ 02, 2018 152

በመካከለኛው ምስራቅ ለሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች እና ለዓለም ኢኮኖሚ መረጋጋት ወሳኝ የሆነው የአሜሪካ እና የኢራን የሰላም ንግግር ቅዳሜ ጠዋት በፓኪስታን መዲና ኢስላማባድ ይጀመራል።
የአሜሪካውን ልዑክ በምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ እና በልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ የሚመራ ሲሆን፣ በኢራን በኩል በይፋ የተነገረ ነገር ባይኖረም ልምድ ያካበቱት የፓርላማ አፈ-ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ውይይት ላለፉት ሳምንታት የቀጠለውን ውጥረትና የነዳጅ ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት የመጀመሪያውና ጠንካራው የዲፕሎማሲ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
ኢራን ባቀረበችው ባለ 10 ነጥብ የሰላም ዕቅድ እና አሜሪካ ባቀረበቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ሰፊ ልዩነቶች ቢኖሩም፣ የድርድሩ መጀመር በራሱ ለዓለም ሰላም ትልቅ የተስፋ ጭላንጭል ሆኖ ታይቷል።
ምንም እንኳን እንደ ሊባኖስና የሆርሙዝ ወሽመጥ ቁጥጥር ያሉ ጉዳዮች በውይይቱ ላይ የራሳቸውን ጥላ ቢያሳርፉም፣ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራናውያን ለስምምነት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን መግለጻቸው ለድርድሩ ስኬታማነት በጎ ምልክት ተደርጓል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል ያሉትን ውስብስብ ልዩነቶች በአንድ የሳምንት መጨረሻ ንግግር ብቻ መፍታት አስቸጋሪ ቢሆንም፣ የኢስላማባዱ መድረክ ጦርነቱን በዘላቂነት ለማቆም የሚያስችል የመንገድ ካርታ ይቀረጽበታል ተብሎ በታላቅ ጉጉት እየተጠበቀ ነው።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህ ንግግር በሰላም ተቋጭቶ ቀጣናው ወደ ቀድሞ መረጋጋቱ እንዲመለስ አይኑን ወደ ፓኪስታን አቅንቷል።
በሃብተሚካኤል ክፍሉ