Search

አሜሪካ እና ኢራን ከ47 ዓመታት በኋላ ፊት ለፊት የሚገናኙበት የኢስላማባድ ታሪካዊ ድርድር

ቅዳሜ ሚያዝያ 03, 2018 81

ለስድስት ሳምንታት የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ጦርነት ለመቋጨት የታለመው ታሪካዊ የሰላም ድርድር ዛሬ በፓኪስታን መዲና ኢስላማባድ በከፍተኛ ጥበቃ መጀመሩ ተገልጿል።
በአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚመራው የአሜሪካ ልዑክ ዛሬ ጠዋት ኢስላማባድ የደረሰ ሲሆን፣ በፓኪስታን ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር አቀባበል ተደርጎለታል።
ይህ ድርድር እ.አ.አ. ከ1979 የኢራን አብዮት በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገ ከፍተኛው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲሆን፣ ከ2015ቱ የኒውክሌር ስምምነት በኋላም ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ይፋዊ የፊት ለፊት ንግግር ነው።
ምንም እንኳን የንግግሩ መጀመር ትልቅ ተስፋ ቢሰጥም፣ የኢራን ልዑክ መሪና የፓርላማ አፈ-ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ዋሽንግተን በሊባኖስ በኩል የተኩስ አቁም ስምምነት እንድታደርግና የታገዱ የኢራን ሀብቶችን እንድትለቅ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው በሂደቱ ላይ ጥላ አሳርፏል።
ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ያላትን ሙሉ ስልጣን እውቅና እንዲሰጣትና የኢኮኖሚ ማዕቀቦች እንዲነሱላት እየጠየቀች ሲሆን፣ አሜሪካ በበኩሏ የሊባኖሱ ጦርነት ከዚህ ስምምነት ጋር እንደማይገናኝና ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እንድታቆም ትፈልጋለች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ኢራናውያን አሁን ላይ የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸውና ስምምነት ላይ መድረስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካው ልዑክ መሪ ጄዲ ቫንስ ለውጤታማ ድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ ኢራን በንግግሩ ላይ የምታሳየው አቋም ተቀባይነት ከሌለው ድርድሩን ለማቋረጥ እንደማያመነቱ አስጠንቅቀዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ እንዲንር እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና የፈጠረው ይህ ግጭት በኢስላማባድ በሚደረገው ድርድር ስምምነት ላይ ይደርስ እንደሆነ መላው ዓለም በትኩረት እየተከታተለው ይገኛል።