ፓኪስታን ከኢራን ጋር በመተባበር ወደ መካከለኛው እስያ ሀገራት የሚወስድ አዲስ የንግድ መስመር በይፋ ማስጀመሯን አስታውቃለች።
ይህ አዲስ የንግድ ኮሪደር ፓኪስታን በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ግጭት ለማርገብና በኢራን እና በምዕራባውያን መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በሰላም ለመፍታት ከምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን የዘርፉ ተንታኞች ገልጸዋል።
የመጀመሪያው የታሸገ የቀዘቀዘ ሥጋ ጭነት ባለፈው ዓርብ ወደ ኡዝቤኪስታን መዲና ታሽከንት መጓጓዙን ተከትሎ፣ የፓኪስታን-ኢራን የትራንዚት ኮሪደር በይፋ ሥራ ጀምሯል።
ይህ የፓኪስታን-ኢራን የንግድ መስመር በቻይና-ፓኪስታን የኢኮኖሚ ኮሪደር (CPEC) ውስጥ የሚገኘውን ስትራቴጂካዊ የጓዳር ወደብን በመጠቀም ሸቀጦችን ወደ መካከለኛው እስያ ሀገራት ለማጓጓዝ የሚያስችል ነው።
በተለይም ፓኪስታን ከቱርክ፣ ቻይና፣ ሳዑዲ ዓረቢያ እና ግብፅ ጋር በመሆን በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የተጫወተችው የአደራዳሪነት ሚና ለሁለቱ ሀገራት የንግድ ትብብር መጎልበት ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉ ተመላክቷል።
በሌላ በኩል ይህ አዲስ መስመር ሕንድ በኢራን በኩል ወደ አፍጋኒስታን እና መካከለኛው እስያ ለመድረስ የነበራትን ተፅዕኖ እንደሚቀንሰው ተገምቷል።
ሕንድ በቻባሃር ወደብ ላይ የነበራትን ተሳትፎ በአሜሪካ ማዕቀብ ሥጋት ምክንያት መቀነሷን ተከትሎ በተፈጠረው የንግድ ክፍተት ፓኪስታን ተጠቃሚ መሆን መቻሏ ተገልጿል።
የፓኪስታን ከመካከለኛው እስያ ሀገራት ጋር ያላት የንግድ ልውውጥ በፈረንጆቹ 2025 ወደ 2.41 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱ የዚሁ ስኬት ማሳያ ተደርጎ መወሰዱን አናዶሉ ዘግቧል።
በለሚ ታደሰ