Search

ስትራቴጂያዊ አይበገሬነት

ማክሰኞ ሚያዝያ 06, 2018 157

ዓለም የምትተነፍስበት የኢኮኖሚ ሳምባ፣ የንግድ መርከቦች የሚርመሰመሱባቸው ውቅያኖሶች እና የኢንዱስትሪዎች ደም ሥር የሆነው ነዳጅ የሚፈስባቸው መስመሮች ዛሬ የውጥረት እና የስጋት መድረክ ከሆኑ ሰንብተዋል።

ይህ ቀጣና የሃይማኖቶች መገኛ እና የባህሎች መገናኛ ብቻ ሳይሆን፣ የዓለምን የኃይል ሚዛን የሚወስን ስትራቴጂካዊ ጨዋታ ሜዳ ነው። ዛሬ በዚህ ቀጣና የተከሰተው መጠነ-ሰፊ ግጭት እና የኃያላን ሽኩቻ፣ ከአካባቢያዊ ወታደራዊ ግጭትነት ባለፈ፣ ለዘመናት የቆዩ የፋይናንስ መዋቅሮችን የሚንድ እና የዓለምን የኢኮኖሚ ደም ሥር የሚበጥስ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል። በዚህ ታላቅ መናወጥ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትከተለው የስትራቴጂካዊ አይበገሬነት መንገድ ለሌሎች ሀገራትም ትምህርት የሚሰጥ አዲስ ምዕራፍ ነው።

የዚህ የኃይል አቅርቦት ቀውስ ማዕከል የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ፣ የዓለምን የነዳጅ ንግድ አንድ አምስተኛ (20 በመቶ ገደማ) የሚያስተላልፍ ቀዳሚው የኢኮኖሚ ደም ሥር ነው። ይህ ሰርጥ መዘጋቱ ወይም አለመረጋጋት ውስጥ መግባቱ በዓለም አቀፍ የኃይል ገበያ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሯል።

የሆርሙዝ ሰርጥ በአንድ ወገን ቁጥጥር ስር ብቻ ሊወድቅ አይገባም የሚሉ ድምፆች እና አስተዳደሩ ዓለም አቀፍ ንግድን በማያስተጓጉል መልኩ እንዲሆን የሚያደርግ ተቋማዊ አሠራር ሊፈጠር ይገባል የሚሉ እሳቤዎች በስፋት እየተንጸባረቁ ይገኛሉ።

ይህ የንግድ መስመር መስተጓጎል በነዳጅ ዋጋ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም የማኑፋክቸሪንግ እና የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ወጪ እንዲቆለል አድርጓል። የሎጂስቲክስ ወጪ መጨመር በቀጥታ ወደ ተለያዩ ሀገራት ውስጥ በሚገቡ ስትራቴጂያዊ ሸቀጦች፣ በተለይም እንደ ነዳጅ እና ማዳበሪያ ባሉ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጫና መፍጠሩ ተስተውሏል። ይህ ሁኔታ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን፣ የሥራ አጥነትን እና የኢኮኖሚ መቀዝቀዝን በማስከተል ዓለምን ወደማይታወቅ የኢኮኖሚ ቀውስ እየገፋት ይገኛል።

ይህ ዓለም አቀፋዊ የነዳጅ አቅርቦት ቀውስ እና የዋጋ መናር፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ነዳጅን ከውጭ የሚያስገቡ ሀገራትን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና ለውስጥ የዋጋ ግሽበት አጋልጧቸዋል። በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ሀገራት የወጪ እና የገቢ ንግዳቸው ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በእነዚህ የባሕር መስመሮች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ የኤክስፖርት ገቢያቸው እንዲቀንስ እና የኢምፖርት ወጪያቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲንር አድርጎታል።

ስትራቴጂያዊ የአይበገሬነት ጉዞ

ይህንን ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ ጫና ለመከላከል እና ሀገራችንን ለማረጋጋት፣ መንግሥት "ስትራቴጂያዊ የኢኮኖሚ አይበገሬነት" (Economic Resilience) አቅምን የመገንባት አቅጣጫ ነድፎ ወደ ተግባር ገብቷል። በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያለውን ጥገኝነት ለመቀነስ ወደ አረንጓዴ ኢነርጂ የሚደረገውን ሽግግር ማፋጠን ዋነኛ ስትራቴጂያዊ ግብ ተደርጓል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን አቅም በመጠቀም፣ የትራንስፖርት እና የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከውጭ ነዳጅ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲዞሩ እየተደረገ ነው። በተለይም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እና የባቡር ትራንስፖርትን ማስፋፋት ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ የአይበገሬነት ግንብ መሆን ችሏል።

ከዚህም ባለፈ፣ የዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች መዘጋት እና የሸቀጦች ዋጋ መናር ሕዝቡን ለችግር እንዳይዳርግ፣ መንግሥት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነት የሚደረገውን የልማት መርሐ-ግብር ሽግግር በሚያስደንቅ ፍጥነት እያፋጠነ ይገኛል።

በውጭ አቅርቦት ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ፣ እንደ ስንዴ እና መሰል የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ በስፋት በማምረት ራስን የመቻል አቅም ተገንብቷል።

የውጭ ንግድ መስመሮች በሚዘጉበት ወቅት መሠረታዊ የኢንዱስትሪ እና የፍጆታ ዕቃዎች እጥረት እንዳይከሰት የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት የገቢ ዕቃዎችን የመተካት ሥራ በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል። በተለይም መድኃኒቶችን፣ የምግብ ሸቀጦችን እና መሠረታዊ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

ወደፊት፦ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የባሕር በር ፍላጎት

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጠረው የዋጋ ግሽበት እና የአቅርቦት ሰንሰለት መቋረጥ በሀገር ውስጥ ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይፈጥር ለመከላከል፣ መንግሥት ለቅጽበታዊ አደጋዎች ምላሽ እና ለስትራቴጂያዊ መጠባበቂያ የሚሆን ጠንካራ የክምችት ሥርዓት በበቂ ሁኔታ መያዝ ጀምሯል። በተጨማሪም ቀይ ባሕር እና የኤደን ባህረ-ሰላጤ የጦር ቀጣና ቢሆኑ እንኳ የኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ እንዳይስተጓጎል፣ አማራጭ የወደብ በሮች እና የንግድ መተላለፊያዎችን የማፈላለግ እና የሎጂስቲክስ መሠረተ-ልማቶችን የማስፋፋት ሥራ በከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቁርጠኝነት እየተከናወነ ይገኛል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የባህር በር የማግኘት መብትን በሰላማዊ እና በሕጋዊ መንገድ ለማረጋገጥ የተጀመረው ትግል፣ የሀገራችንን የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ደኅንነት ለማረጋገጥ የታለመ ስትራቴጂያዊ እርምጃ ነው።

በአጠቃላይ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሆርሙዝ ሰርጥ የተከሰተው ቀውስ ለኢትዮጵያ ከባድ ፈተና ቢሆንም፣ መንግሥት ይህንን ጫና ወደ ውስጥ የመመልከት እና ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር ጥበብን በተግባር አሳይቷል።

ጦርነቱ የደቀነውን የኢኮኖሚ አደጋ በመመከት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ አቅምን በማጎልበት፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መናወጥ ውስጥም የማይበገር የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ሥርዓት በመገንባት ላይ ትገኛለች። ይህ የስትራቴጂካዊ አይበገሬነት ጉዞ፣ ኢትዮጵያን በነገዋ ዓለም ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪና በራሷ የምትተማመን ታላቅ ሀገር የማድረግ ግብን ያሳካል።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

#EBC #Ethiopia #sovereignty #resilience