የእስራኤል እና የሊባኖስ መሪዎች ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን ቀጥተኛ ግንኙነት በማደስ፣ በዛሬው ዕለት ታሪካዊ የተባለለትን ንግግር እንደሚያደርጉ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በራሳቸው የትሩዝ ሶሻል ገጽ ላይ ባሰፈሩት መረጃ፤ ሁለቱ ሀገራት ከ34 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ቀጥተኛ ንግግር የሚመጡት በቀጠናው ሰላም ለማስፈን እየተደረገ ካለው ጥረት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በመልዕክታቸው “በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የተወሰነ የእፎይታ ጊዜ ለመፍጠር እየሞከርን ነው፤ ይህም መልካም ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
እንደ ቴሌግራፍ ዘገባ ይህ የመሪዎቹ ንግግር ይፋ የተደረገው የሁለቱ ሀገራት መልዕክተኞች በዋሽንግተን ዲሲ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ካደረጉ በኋላ ነው።
በተለይም ባለፈው ማክሰኞ የሁለቱ ሀገራት አምባሳደሮች በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት ያልተለመደ ቀጥተኛ ስብሰባ በቤይሩት ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለማቆም እና የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመ እንደነበር ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለ ስብሰባው ዝርዝር ሁኔታ እና ስለሚካሄድበት ቦታ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም፣ ውይይቱ መካሄዱ በራሱ በመካከለኛው ምስራቅ ለረጅም ጊዜ ለቆየው ውጥረት አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ሊከፍት እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ