ታሪክ ራሱን የሚደግምበት ሳይሆን አዲስ ምዕራፍ የሚወልድበት አስገራሚ የታሪክ መጋጠሚያ ላይ እንገኛለን። ዛሬ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚታየው ሁኔታ የቀጣናዊ ግጭት ውጤት ብቻ ሳይሆን፤ ለዘመናት የቆየው የዓለም የኃይል ሚዛን እየተናወጠ አዲስ ሥርዓት እየተቀረጸ መሆኑን የሚያሳይ ምጥ ነው። ይህ ቀጣና የኃያላን የስበት ማዕከል እንደመሆኑ፤ የሚነሳው ማዕበል ንዝረት መላውን ዓለም ይዳስሳል።
የአሁኑ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ካለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት እጅግ የተለየና ውስብስብ ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለምን በሕግና በሥርዓት ይመራሉ ተብለው የተገነቡት እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የዓለም አቀፍ ፍትህ ፍርድ ቤት ያሉ ተቋማት፣ ዛሬ የሰላም ማስከበር አቅማቸውና ተሰሚነታቸው እየላላ መጥቷል። ይህ ተቋማዊ መዳከም ሀገራት በሕግ ከመተማመን ይልቅ ወደ ኃይል ፖለቲካና ወደ ግል ጦር መሣሪያ ክምችት እንዲያዘነብሉ በማድረግ ዓለምን ወደ "የጫካ ሕግ" ሥርዓት እየመለሳት ይገኛል።
በዲፕሎማሲው መድረክ የሚታየው የዋልታ ረገጥነት ሀገራት በአንዱ ጎራ እንዲሰለፉ ጫና እየፈጠረ ሲሆን፤ ከዚህም ባሻገር እውነትና ሐሰት በማይለይበት የድህረ-እውነት (post-truth) ዘመን ውስጥ የመረጃ ማዛባት፣ የሳይበር ጥቃትና ሥነ-ልቦናዊ ጫናዎች አዲሱ የጦርነት ግንባር ሆነዋል። ይህ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረት ማዕበል የዓለምን የኢኮኖሚ ደም ሥሮች ነክቷል። በተለይም እንደ ሆርሙዝ ሰርጥና ቀይ ባሕር ያሉ ስትራቴጂካዊ የንግድ መስመሮች የጦር ሰፈር መሆናቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ፣ የሸቀጦችና የማዳበሪያ ዋጋን በማስወንጨፍ አደገኛ የዋጋ ግሽበትን ፈጥሯል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የፔትሮ-ዶላር ሥርዓት ታሪካዊ የበላይነት እየተፈተነ ዓለም ወደ ባለብዙ የገንዘብ ሥርዓት አማራጮች ማምራቷ፣ በዓለም የፋይናንስ ፍሰት ላይ ከፍተኛ መዋዠቅ ማስከተሉ አልቀረም።
በዚህ እጅግ ኢ-ተገማች በሆነ ሁኔታ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትከተለው ጎዳና ግልጽና መርህ ተኮር ነው። መንግሥት የትኛውንም ጎራ ሳይወግን፣ ብሔራዊ ጥቅምንና ሉዓላዊነትን ማዕከል ያደረገ ሚዛናዊና ነፃ ዲፕሎማሲን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። የጎራ ፖለቲካ ጫናዎችን በብልሃት በመቋቋም፣ ከሁሉም ጋር ያለውን ግንኙነት ሳይሸረሽር ከብሪክስ (BRICS+) ሀገራት ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር አማራጮችን እያሰፋ ነው። ዓለም አቀፍ ተቋማት በሚዳከሙበት በዚህ ወቅት፣ ቀጣናዊ ችግሮችን በራስ አቅም ለመፍታት እንደ ኢጋድና የአፍሪካ ሕብረት ያሉ ተቋማት ሚና እንዲጎለብት ማድረግ የመንግሥት ቁልፍ ስትራቴጂ ሆኗል።
ከኢኮኖሚ አንፃር ኢትዮጵያ የዓለምን የንግድ መስተጓጎል ለመቀልበስ የኢኮኖሚ አይበገሬነትን (Economic Resilience) መገንባት እንደ ብቸኛ የህልውና አማራጭ ወስዳ እየሰራችበት ይገኛል። መንግሥት ሀገራችንን ከዕርዳታ ጥገኝነት ወደ ማምረት አቅም በማሸጋገር፣ የግብርና ምርቶችን በተለይም ስንዴንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ተጽዕኖን ለመቀነስ ሰፊ ርብርብ እያደረገ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ የኢኮኖሚ ነፃነትና የዘላቂ ብልፅግና ዋስትና የሆነውን አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት መብት በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት የማይቀለበስ ታሪካዊና መንግሥታዊ አቅጣጫ ነው።
በመከላከያና ደኅንነት ዘርፍም፣ ዘመናዊ ጦርነት የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ የበላይነት ለመቆናጠጥ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው። የሀገር ሉዓላዊነት በሰው ኃይል ብዛት ብቻ ሳይሆን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሳይበር ደኅንነትና በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ቴክኖሎጂ ጭምር የሚረጋገጥ በመሆኑ፤ የፀጥታ ተቋማትን የማዘመንና የባሕር ኃይልን የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በተጓዳኝም፣ ዓለም አቀፍ ቀውሶችን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ሀገርን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎችንና የሐሰት መረጃዎችን በመመከት፣ የዜጎችን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ማጠናከር የመንግሥት ቀዳሚ የቤት ሥራ ሆኗል።
ዓለም በማይታወቁ ጂኦ-ፖለቲካዊ ማዕበሎች ውስጥ በምትናወጥበት በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ዋስትናው በውጭ ኃይሎች በጎ ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን በሀገር ውስጥ በሚገነባ ጠንካራ የኢኮኖሚና የመከላከል አቅም ላይ ብቻ ነው። መንግሥት የገጠሙትን ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች ወደ ዕድል በመቀየር፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥና የዜጎችን አንድነት በማጽናት ኢትዮጵያን በባለብዙ ዋልታ ዓለም ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪና ታላቅ ሀገር ለማድረግ በሚያስችል ብሩህ ጎዳና ላይ ይገኛል። ይህ ጉዞ የሁላችንንም ጽናትና አንድነት የሚጠይቅ የታሪክ አደራ ነው።
በአዶኒያስ ወደልአረጋይ