Search

የአውሮፓ ኅብረት የአውሮፕላን ነዳጅ እጥረት ለመቋቋም የሚያስችል ዕቅድ ይፋ ሊያደርግ ነው

ሓሙስ ሚያዝያ 08, 2018 105

በመካከለኛው ምስራቅ አሜሪካ እና እስራኤል ከኢራን ጋር የገቡበት ጦርነት በአውሮፓ አየር መንገዶች ላይ የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ስጋት ደቅኗል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍም የአውሮፓ ኅብረት ልዩ የመፍትሄ ዕቅድ እያዘጋጀ መሆኑን የህብረቱ ባለሥልጣናት መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ኅብረቱ የነዳጅ ማጣሪያዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግና የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማረጋጋት የሚያስችል ረቂቅ ሰነድ እያዘጋጀ ይገኛል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ በአባል ሀገራቱ የሚገኙ የነዳጅ ማጣሪያዎችን የማምረት አቅም በዝርዝር የሚያጠና ሲሆን፣ ያሉትን ማጣሪያዎች ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል።
አውሮፓውያን 75 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ የሚያስመጡት ከመካከለኛው ምስራቅ በመሆኑ፣ ኅብረቱ አሁን ላይ የገጠመውን እጥረት ለመቅረፍ አማራጭ መፍትሄዎችን ለመመልከት ተገዷል።
ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ (IEA) በበኩሉ አውሮፓ ከመካከለኛው ምስራቅ የሚያገኘውን ነዳጅ ቢያንስ በግማሽ መተካት ካልቻለ፣ እስከ ሰኔ ወር ድረስ የክረምቱን የጉዞ ወቅት የሚያስተጓጉል ከፍተኛ እጥረት ሊያጋጥመው እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።
በመሀመድ ፊጣሞ