በኢራን እና በአሜሪካ መካከል እየተካሄደ ያለው ድርድር አካል የሆነ አዲስ የመፍትሔ ሐሳብ መቅረቡን ለቴህራን ቅርብ የሆኑ ምንጮች ገለጹ።
እንደ ምንጮቹ ጥቆማ ከሆነ፣ ኢራን በቀጣይ ጦርነት እንደማይቀሰቀስ የሚያረጋግጥ ዘላቂ ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ የኦማን ወገን ያለ ምንም የጥቃት ስጋት በነፃነት እንዲጓዙ የመፍቀድ ፍላጎት አላት።
በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ኢራን በወሽመጡ በኩል የሚደረገውን የባሕር ላይ ትራፊክ በማስተጓጎሏ ምክንያት፣ በዓለም አቀፍ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩ ይታወቃል።
ጦርነቱ ካለፈው የካቲት ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች እና ወደ 20,000 የሚጠጉ መርከበኞች በባሕረ ሰላጤው ውስጥ እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል።
ምንም እንኳን ባለፈው መጋቢት መጨረሻ የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈጻሚ ቢሆንም፣ በወሽመጡ ላይ ያለው የቁጥጥር ጉዳይ አሁንም በድርድሩ ጠረጴዛ ላይ ዋነኛው አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ረቡዕ ጦርነቱ ሊያበቃ መቃረቡን ቢገልጹም፣ በስትራቴጂካዊው መስመር ላይ ያለው ውጥረት ግን ገና አልረገበም።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ምንጭ ብሎ ሮይተርስ እንደዘገበው ኢራን መርከቦች በኦማን የባሕር ክልል በኩል ያለ ምንም እንቅፋት እንዲጓዙ ፈቃደኛ ልትሆን ትችላለች።
ይሁን እንጂ ቴህራን በአካባቢው የተቀበሩ የባሕር ላይ ፈንጂዎችን ለማንሳት መስማማቷን እና ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን መርከቦች ጨምሮ ለሁሉም ወገኖች እኩል ፈቃድ ስለመስጠቷ እስካሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።
ይህ የኢራን ይሁንታ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ተስፋን የፈነጠቀ ቢሆንም፣ የድርድሩ ውጤት ግን አሁንም በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ