Search

የብሪክስ ሀገራት የጤና ትብብርን ለማጠናከር አዲስ አጀንዳ ይፋ አደረጉ

ዓርብ ሚያዝያ 09, 2018 125

የብሪክስ አባል ሀገራት በሕዝብ ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል አዲስ አጀንዳ ይፋ አደረጉ። ሕንድ የ2026 የብሪክስ የጤና አጀንዳን ይፋ ባደረገችበት የመጀመሪያው የሥራ ቡድን ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል ሀገራቱ በንቃት በመሳተፍ የቀረቡትን የትብብር አቅጣጫዎች ደግፈዋል።

የሕንድ የጤና እና ቤተሰብ ደኅንነት ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ፑንያ ሳሊላ ስሪቫስታቫ ስብሰባውን በከፈቱበት ወቅት፣ የብሪክስ ፕሬዝዳንትነት በፈረንጆቹ 2026 አካታች እና በማስረጃ ላይ የተመሰረተ የጤና ትብብርን እንደሚያስቀድም ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ሦስት ግዙፍ የውሳኔ ሐሳቦች ቀርበው ተቀባይነት አግኝተዋል፦

  • የጤናማ አኗኗር ተልዕኮ፦ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብንና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማነስን በመከላከል፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን (NCDs) ጫና በጋራ ለመቀነስ፤

  • የአእምሮ ጤና እና ደኅንነት፦ የአእምሮ ጤና አገልግሎቶችን በአጠቃላይ የጤና ሥርዓቶች ውስጥ በማካተት ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ፤

  • የባህላዊ ሕክምና ምርምር፦ በሀገር በቀል ዕውቀት ላይ የተመሰረተውን ባህላዊ ሕክምና በሳይንሳዊ ማስረጃ በማሳደግ ለአጠቃላይ የጤና ሽፋን እንዲውል ለማድረግ የሚሉት ናቸው።

ሀገራቱ ከአዳዲሶቹ አጀንዳዎች ባሻገር፣ የወደፊት የጤና ስጋቶችን ለመከላከል በሚያስችሉ ስልቶች ላይም ተስማምተዋል። ከእነዚህም መካከል ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የተቀናጀ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት መዘርጋት እና የታካሚዎችን መረጃ ለማስተሳሰር የሚያስችል የዲጂታል ጤና ሥነ-ሕንጻ ልማት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በስብሰባው ላይ የተሳተፉት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን አባላት በአጀንዳዎቹ ላይ ያላቸውን ድጋፍ የገለጹ ሲሆን፣ በተለይም ባህላዊ ሕክምናን የማዘመንና ወደ ብሔራዊ የጤና ሥርዓት የማስገባት ሐሳብ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ተመልክቷል። ስብሰባው በ2026 የብሪክስ የጤና ተነሳሽነት ስር ለሚከናወኑ የቴክኒክ ምክክሮች እና የሚኒስትሮች ደረጃ ውይይቶች ፍኖተ ካርታ በማስቀመጥ ተጠናቋል።

በሰለሞን ገዳ