Search

የጂኦ-ፖለቲካዊ ለውጦች እና ኢትዮጵያዊ ብልህነት

ቅዳሜ ሚያዝያ 10, 2018 167

ዓለማችን ዛሬ ካለፉት ዐሥርተ ዓመታት በበለጠ እጅግ ውስብስብ፣ ተለዋዋጭ እና አስገራሚ በሆኑ የጂኦ-ፖለቲካዊ ሽግግሮች ውስጥ ትገኛለች።

የቀድሞው የዓለም የኃይል አሰላለፍ እየተቀየረ፣ አዳዲስ ኃይሎች ብቅ እያሉ እና ነባር ስምምነቶች እየፈረሱ ባለቡበት በዚህ የታሪክ ምዕራፍ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ስልታዊ ቦታ ላይ የሚገኙ ሀገራት የጥንቃቄና የብልህነት ጉዟቸው የኅልውና ጉዳይ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በዚህ በፈተናዎች እና በዕድሎች በተሞላው የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ማዕበል ውስጥ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስከበር እና የቀጠናውን ሰላም በማረጋገጥ ረገድ እያሳየችው ያለችው "ኢትዮጵያዊ ብልህነት" ለብዙዎች ተምሳሌት የሚሆን ነው።

የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት እና የሆርሙዝ ሰርጥ ስጋት

የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና የታሪክ፣ የሃይማኖት እና የዓለም የኢኮኖሚ ደም ሥር የሆነው የኃይል ምንጭ ማዕከል ነው። በዚህ ቀጣና የሚከሰት ማንኛውም ግጭት ዓለምን የማናወጥ አቅም አለው። በተለይም የሆርሙዝ ሰርጥ ጉዳይ የዓለም የጂኦ-ፖለቲካ ትኩረት ሆኖ ቆይቷል።

በዓለም ላይ ካለው የነዳጅ ንግድ አንድ አምስተኛው የሚተላለፍበት ይህ ሰርጥ፣ ትላንት ክፍት ሆኖ የዓለምን ኢኮኖሚ ሲያሽከረክር ቆይቶ፣ ዛሬ ደግሞ በኃያላን ሀገራት ፍጥጫ እና በክፍለ-ቀጣናው ውጥረት ምክንያት "ሊዘጋ ይችላል" የሚለው ስጋት ከፍ ብሏል።

ኢትዮጵያ እንደ አንድ በማደግ ላይ ያለች ሀገር እና የነዳጅ ምርትን ከውጭ እንደምታስገባ ሀገር፣ የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ እንድምታ በቀጥታ የዜጎቿን የዕለት ተዕለት ሕይወት ሲነካ ቆይቷል።

የነዳጅ ዋጋ መናር፣ የሎጂስቲክስ መጓተት እና የዋጋ ንረት ተከታይ ውጤቶች ናቸው። ሆኖም ኢትዮጵያ ይህንን ስጋት ለመቋቋም የያዘችው ብልህ መንገድ "የመከላከያ ዲፕሎማሲን" እና "ኢኮኖሚያዊ ዝግጅትን" ያጣመረ ነው።

በቅርቡ የተመረቀው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ በታዳሽ ኃይል ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት፣ ሀገራችን በነዳጅ ላይ ያላትን ጥገኝነት በመቀነስ ለጂኦ-ፖለቲካዊ ድንገተኛ አደጋዎች የምትሰጠው ስልታዊ ምላሽ አካል ነው።

ኢትዮጵያዊ ብልህነት፡ ሚዛናዊነት እና ብሔራዊ ጥቅም

ኢትዮጵያ በለውጥ ዓመታት ውስጥ የተከተለችው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ "መደመርን" ማዕከል ያደረገ ነው። ይህ ዕሳቤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉም ወገን አሸናፊ የሚሆንበት ግንኙነት ይተልማል። ዓለም በምዕራባውያን እና በምሥራቃውያን ጎራ በሚከፈልበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በአንዱ ወገን ተሰልፋ የሌላውን ጥላቻ ከማትረፍ ይልቅ፣ የሁሉንም ወዳጅነት የምትሻ እና ብሔራዊ ጥቅሟን በየትኛውም መድረክ የምታስከብርበትን "ሚዛናዊ ዲፕሎማሲ" መርጣለች።

የብሪክስ (BRICS+) አባልነት የዚህ ብልህነት ትልቅ ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ ከነባር ወዳጆቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ሳታሻክር፣ ከአዳዲስ የኢኮኖሚ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ አማራጭ የልማት ፋይናንስና የገበያ ዕድሎችን ለመፍጠር መቻሏ የዲፕሎማሲ ልዕልናዋን ያሳያል። ይህ አባልነት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ ያላትን ድምፅ ከፍ ከማድረጉም ባለፈ፣ በጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎች ወቅት እንደ መከታ ያገለግላታል።

የባህር በር ፍላጎትና ቀጠናዊ ትስስር

ሌላኛው የኢትዮጵያዊ ብልህነት መገለጫ የወደብና የባህር በር ጥያቄን ወደ ጠረጴዛ ማምጣቷ ነው።

130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር የባህር በር አልባ ሆና መቅረቷ የኢኮኖሚ እድገቷንና ሉዓላዊነቷን እንደሚገድበው በመረዳት፣ መንግሥት ለቀጣናዊ ትስስር የሚጠቅሙና ለጎረቤት ሀገራትም የጋራ ጥቅም የሚያስገኙ ስምምነቶች ላይ ትኩረት አድርጓል።

ይህ ጥያቄ የግጭት ሳይሆን የልማት፣ የመጠፋፋት ሳይሆን የመደመር ጥያቄ መሆኑን በዓለም አቀፍ መድረክ ማስረዳት መቻሏ የብልህ አመራር ውጤት ነው።

ሰላም እንደ መሠረት፡ የውስጥ ጥንካሬ ለውጭ ተፅዕኖ

ኢትዮጵያ የጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎችን ለመቋቋም ትልቁ መሣሪያዋ የውስጥ ሰላሟ መሆኑን ተረድታለች። የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋም ኢትዮጵያ ችግሮቿን በራሷ አቅምና በ"አፍሪካዊ መፍትሔ" ለመፍታት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያሉ። የውስጥ አንድነት ሲጠናከር፣ የውጭ ኃይሎች በሀገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ዕድላቸው እየጠበበ ይሄዳል። ይህ የሰላም ስምምነት ጥረት ኢትዮጵያን በቀንድ አፍሪካ የሰላም አምባሳደርነቷን ዳግም ያረጋገጠላትና ዓለም አቀፍ አመኔታን እንድታገኝ ያደረገ ስኬት ነው።

መፃኢ ዕድል፡ ብሩህ አድማስ

ኢትዮጵያ ዛሬ በያዘችው ብልህ መንገድ፣ በጂኦ-ፖለቲካዊ ሽግግሮች ውስጥ ተገፊ ሳይሆን ተዋናይ ሆና ብቅ ብላለች። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ የስንዴ ኤክስፖርት፣ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄና የታዳሽ ኃይል ልማቶች ሀገሪቱ በራሷ አቅም ለመቆም የምታደርገውን ጥረት የሚያሳዩ  ፍሬዎች ናቸው።

በመካከለኛው ምሥራቅ የሚከሰቱ ውጥረቶችና እንደ ሆርሙዝ ያሉ ስትራቴጂካዊ ቦታዎች ስጋት ቢሆኑም፣ ኢትዮጵያ ግን በ"መደመር" ፍልስፍና የታነጸ፣ በብሔራዊ ጥቅም የተቃኘና በሰላም ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ መንገድን በመከተል ፈተናዎችን ወደ ዕድል እየቀየረች ትገኛለች።

ይህ ኢትዮጵያዊ ብልህነት ሀገሪቱን ወደ ላቀ የልዕልና ማማ ላይ የሚያወጣና ለሚመጣው ትውልድ የምትኮራባትን፣ የበለፀገችና ሉዓላዊነቷ የተከበረ ሀገርን ለማውረስ ዋስትና የሚሆን ነው።

በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል በዛሬው ብልህ እርምጃዎቿ ላይ የተመሠረተ ነው። ዓለም ቢናወጥም፣ ኢትዮጵያ በጽናትና በጥበብ ጉዞዋን ትቀጥላለች፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ዐዲሲቷ የተስፋ ዓድማስ ናትና!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ