Search

ኢትዮጵያን አስደናቂ የቱሪስት መዳረሻዎች ያስቃኘው የሳዑዲ ልዑካን ቡድን ጉብኝት

ቅዳሜ ሚያዝያ 17, 2018 329

ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ፣ የታሪክና የባህል ማራኪ መስህቦች ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ያለመው የሳዑዲ ዓረቢያ የቱሪዝም ልዑካን ቡድን የትውውቅ ጉብኝት በስኬት ተከናውኗል።
በሪያድ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከቱሪዝም ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የሳዑዲ ዓረቢያ የቱሪዝም ልዑካን ቡድን ጉብኝት፣ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ውበቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በስፋት እንዲተዋወቁ አመቺ ዕድል ፈጥሯል።
ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎችን፣ ጋዜጠኞችን እና የጉዞ ወኪሎችን ያቀፈው ይህ ልዑክ፤ ከአዲስ አበባ ዘመናዊ ፓርኮች እስከ ጥንታዊቷ ሐረር የጀጎል ግንብ ድረስ ያለውን አስደናቂ ሀብት በአካል ተመልክቷል።
ይህ ጉብኝት ለኢትዮጵያ ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር ሲታይ፣ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ጥቅሎች ለሳዑዲና ለባህረ-ሰላጤው ሀገራት በጠቅላላው ለዓለም ሕዝብ በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በቆይታቸው የእንጦጦ እና የአንድነት ፓርኮችን፣ የቢሾፍቱን ዘመናዊ ሪዞርቶች፣ የድሬዳዋን ታሪካዊ የባቡር ጣቢያ እና የሐረርን ልዩ ባህላዊ እሴቶች የጎበኙት ልዑካኑ፤ የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ ለተከታዮቻቸው የሚያጋሩበት ዕድል ተፈጥሯል።
በተጨማሪም በሁለቱ ሀገራት የጉዞ ወኪሎች መካከል የተፈጠረው የቀጥታ የቢዝነስ ትውውቅ የቱሪስት ፍሰቱን እንደሚያሳድገው ይታመናል።
ከንግድ ትስስሩ ባለፈ፣ ልዑካኑ በቆይታቸው የታዘቡት "የኢትዮጵያን ለጋስ አቀባበል" እና የተፈጠረው የቤተሰባዊነት መንፈስ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲውን ወደ ላቀ ደረጃ እንዳሸጋገረው የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
ይህ ስኬታማ ጉብኝት ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም ለሀገራዊ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ የሚያግዝ መሆኑም ተጠቁሟል።