የቻይንኛ ቋንቋን በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ለአምስት ዓመታት ለማካተት የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈረመ።
የቻይንኛ ቋንቋ የትምህርት ትብብር ስምምነቱን የትምህርት ሚኒስትር ድኤታው ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቺን ሃይ በጋራ ፈርመውታል።

ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ከማሳደግ በዘለለ በቱሪዝም፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር እና በሌሎች ዘርፎች ላይ የሚኖረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ሚኒስትር ድኤታው ጠቁመዋል።
በተለይም ቻይና ለኢትዮጵያውያን በሚታመቻቸው የስኮላርሺፕ ዕድል አማካኝነት፣ ሀገሪቱ የላቀ ደረጃ ላይ በደረሰችበት የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ቴክኖሎጂ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር የዕውቀት ልውውጥ ለማድረግ ስምምነቱ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቺን ሄ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ እንዲሁም በፍጥነት እያደገ የመጣውን የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ አክለውም በአሁኑ ወቅት በቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የአማርኛ ቋንቋን ማስተማር መጀመሩ የሀገራቱን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ያጠናከረና አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልጸዋል።