Search

የዲጂታል ዘመኑን "ቫይረስ"፦ ሐሰተኛ መረጃን እንዴት እንከላከል?

ረቡዕ ሰኔ 03, 2018 57

በአሁኑ የቴክኖሎጂ ዘመን በኪሳችን በያዝነው ስልክ አማካኝነት በዓለም ዙሪያ የሚከሰቱ ኩነቶችን በቅጽበት ማወቅ እንችላለን። ይሁን እንጂ ይህ የመረጃ ፍሰት የራሱን አደገኛ ፈተና ይዞ መጥቷል፤ ይህም የሐሰት መረጃ (Misinformation/Fake News) መስፋፋት ነው።

የሐሰት ዜናዎች እውነተኛ መረጃዎችን አስመስለው በመቅረብ ህዝብን ለማሳሳት፣ ለማደናገር እና ለተለያዩ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እንዲውሉ ተደርገው የሚቀነባበሩ የዘመናችን “ቫይረሶች” ናቸው።

የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለሐሰተኛ መረጃዎች መፈልፈያና መሰራጫ ዋነኛ መንገዶች ሆነዋል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት የማህበራዊ ሚዲያዎች “አልጎሪዝም” አሰራር ነው። እነዚህ መድረኮች ብዙ መስተጋብር (Interaction) የሚፈጥሩ፣ ሰዎችን የሚያከራክሩና ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ መረጃዎችን ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰራጩ ያደርጋሉ።

የሐሰት ወሬዎች የሰዎችን የፍርሃት፣ የቁጣ ወይም የድንገተኛ ደስታ ስሜት እንዲቀሰቅሱ ተደርገው ስለሚሰሩ፣ ብዙዎች መረጃውን ከማረጋገጣቸው በፊት ለሌሎች እንዲያጋሩት ይገፋፋሉ። ሌላው ትልቁ ምክንያት የዲጂታል እውቀት ማነስ ነው። ብዙ ሰዎች በኢንተርኔት ላይ ያዩት ነገር ሁሉ እውነት የሚመስላቸው በመሆኑ፣ እውነተኛ መረጃን ከሐሰተኛው ለመለየት ይቸገራሉ።

የሐሰት መረጃዎች በሀገርና በሰው ህይወት ላይ ሊመለስ የማይችል ጉዳት ያደርሳሉ። ሆን ተብለው የተቀነባበሩ ታሪኮችና የተሰነባበሩ ምስሎች ለህዝባዊ አመጽ፣ ለዘርና ለሃይማኖት ግጭቶች መነሳሳት ምክንያት ይሆናሉ። ግለሰቦችም የባህሪ ግድያ ሰለባ ይሆናሉ።

እነዚህ ወሬዎች በህዝብና በመንግስት ተቋማት መካከል ያለውን እምነት ያጠፋሉ። ህዝቡ የትኛው እውነት የትኛው ሐሰት እንደሆነ መለየት ሲያቅተው ለተሳሳቱ ውሳኔዎች ይጋለጣል፤ ይህም ማህበራዊ መረጋጋትን ይነሳል።

የሐሰት ወሬዎችን መከላከል የአንድ ወገን ስራ ብቻ ሳይሆን የመገናኛ ብዙሃን፣ የሲቪክ ማህበራት እና የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው። የሚከተሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ የሐሰት መረጃን ስርጭት መግታት ይችላሉ፡-

ቆም ብለው ያስቡ፦  ማንኛውንም መረጃ ከማጋራቶዎ በፊት መረጃው ምን ያህል እውነት ሊሆን እንደሚችል ራስዎን ይጠይቁ። "ይህ መረጃ ሊሆን ይችላል?" የሚለው ጥያቄ የብዙዎችን ህይወት ይታደጋል።

ምንጭን ያረጋግጡ፦  መረጃው የመጣው ከታማኝ የዜና ተቋማት ነው ወይስ ማንነቱ ካልታወቀ ገጽ? ሁልጊዜም የመንግስት ድረ-ገጾችን እና ኦፊሴላዊ መግለጫዎችን ማረጋገጫ ለማግኘት ይጠቀሙ።

ስሜታዊ አይሁኑ፦  አንድ መረጃ እጅግ የሚያስቆጣ ወይም የሚያስደነግጥ ከሆነ፣ ሆን ተብሎ ስሜትዎን ለመቀስቀስ የተሰራ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በስሜት ተገፋፍተው መረጃ አያጋሩ።

ሐሰተኛ መረጃን ሪፖርት (Report) ያድርጉ፦ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተሳሳተ መረጃ ሲያገኙ ለሚመለከተው ኩባንያ ሪፖርት በማድረግ ስርጭቱን እንዲቆም ያድርጉ።

ዲጂታል እውቀታችንን ማሳደግና ለማንኛውም መረጃ ንቁ መሆን የዘመኑ ግዴታ ነው። ማንኛውንም መረጃ ከማሰራጨታችን በፊት ምንጩን ማረጋገጥና በባለስልጣናት የሚሰጡ መመሪያዎችን ብቻ መከተል ይገባል። የእርስዎ ጥንቃቄ የብዙዎችን ህይወት ሊታደግና ሀገርን ከቀውስ ሊጠብቅ ይችላል።