Search

የ5ቱ ዓመታት ገፆች፡ የሚያጎርሱ ሩህሩህ እጆች

ረቡዕ ሰኔ 03, 2018 57

ካለፈው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ አንስቶ ወደ 7ኛው ምርጫ ዋዜማ ስንሸጋገር፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በወርቅ ቀለም ደምቀው ከሚታዩት ገፆች መካከል አንዱና ዋነኛው ሰውን ማዕከል ያደረገው ታላቅ የልማት ስራ ነው።

የመደመር ትውልድ "ሰውን የዘነጋ ልማት የጥፋት ያህል ነው" በሚል ጽኑ የሞራል እሳቤ፣ የልማት ትርጓሜን ከረዣዥም ኮንክሪትና ከአስፋልት ንጣፍ ባሻገር ወደ ዜጎች ማዕድ ላይ አምጥቶታል። ልማት ትርጉም የሚኖረው የነዋሪውን በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናትን ህይወት ሲታደግ ነው በሚል መርህ፣ የመንግስት የትኩረት ማዕከል ወደ ሰው ተመልሷል።

የዚህ ሰው-ተኮር እሳቤ ቁንጮና አስደናቂ ስኬት የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ነው። ትላንት በባዶ ሆዳቸው ትምህርት ቤት እየዋሉ አዕምሯቸው በረሃብ ይዝል የነበሩ፣ በርሀብ ይወድቁ የነበሩ ህፃናትን ታሪክ የመደመር ትውልድ  ቀልብሶታል።

ትናንት ከቤታቸው ሲወጡ አንጀታቸው እየተላወሰ፣ ትምህርት ገበታ ላይ በድካም ይወድቁ የነበሩ ህፃናትን የሰቆቃ ታሪክ ዛሬ ታሪክ ሆኗል፡፡ "መጪው ትውልድ የኔ ነው" ብሎ በሃላፊነት መንፈስ የተነሳው ይህ ትውልድ፣ ቢያንስ ለመማር ተማሪው ምግቡንና የትምህርት ቁሳቁሱን እንዳይቸገር በሚል ርኅራኄ በተሞላበት አቋም ይህን የተቀደሰ ዘመቻ ጀመረ። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ትኩስና የተመጣጠነ ምግብ በትምህርት ቤታቸው እንዲያገኙ ተደርጓል።

ይህ ፕሮግራም የመንግስትን የልማት አቅጣጫ ከማሳየት ባለፈ፣ ኢትዮጵያዊውን የመረዳዳት እሴት በላቀ ደረጃ ያነቃቃ ሆኗል። ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ያደረጉት የተማሪዎች ምገባ ርኅራኄን ተቋማዊ በማድረግ፣ ዜጎች እርስ በእርሳቸው እንዲተጋገዙና የሚያስችል የእሳቤ መሰረት ተጥሏል።

ከምገባው ጎን ለጎንም የትምህርት ቁሳቁሶችን፣ ደብተሮችን እና የደንብ ልብሶችን በነፃ በማቅረብ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰብ ልጆች የኑሮ ጫና ሳይበግራቸው ከሌሎች እኩዮቻቸው ጋር በእኩልነት እንዲማሩ ታላቅ መደላድል ተፈጥሯል።

በዚህም በጠዋት ተነስተው "ልጄ ምን በልቶ ይውላል?" የሚለው የድሃ እናቶች የዘወትር ጭንቀት ቀልሏል። የልጆች የስነ-ልቦና ስብራት ተጠግኖ፣ የሀብታምም ሆነ የድሃ ልጅ አንድ አይነት የደንብ ልብስ ለብሰው፣ ከአንድ ማዕድ እየተመገቡ የመደመርን ትክክለኛ ትርጉም በትምህርት ቤታቸው ግቢ ውስጥ መኖር ችለዋል።

የተማሪዎች ምገባ ስራ ፋይዳው ዛሬ ሆድን ከመሙላትም እጅግ የዘለለ ነው። ይህ ተግባር የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከብ፣ በአካልና በአእምሮ የዳበረ፣ ጤናማና ብቁ ትውልድ የመፍጠር ጥልቅ ሀገራዊ ራዕይ ያለው ተግባር ነው።

በልጅነት ዕድሜ የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት ለአእምሮ እድገት ወሳኝ በመሆኑ፣ የዛሬው ምገባ የነገውን የምርምር፣ የፈጠራና የአመራር አቅም ማጎልበት ማለት ነው። በርሃብ ምክንያት ከትምህርት ገበታ የሚቀሩ ተማሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰ ሲሆን፣ የትምህርት አቀባበላቸውና ውጤታቸውም የዚያኑ ያህል ሊሻሻል ችሏል።

በአጠቃላይ፣ እነዚህ የ5ቱ ዓመታት ገፆች የመደመር ትውልድ ፖለቲካን ከሰብዓዊነት ጋር ያዋሀደበት፣ የነገን ትውልድ በዛሬ ርኅራኄ ያነፀበት ደማቅ የታሪክ ምዕራፍ ናቸው። ፖለቲካ ማለት የስልጣን ሽኩቻ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን እንባ ማበስና የተራቡትን ማጉረስ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።