ታሪክ በየዘመናቱ ማህፀን ውስጥ የየራሱን ጀግኖች ይፀንሳል፣ ይወልዳልም። የትላንቱ ትውልድ ሀገርን ከባዕድ ወራሪ ታድጎ፣ ነፃነቷን በደሙና በአጥንቱ አስጠብቆ የራሱን የዘመን ተልዕኮ ፈፅሞ አልፏል።
የዛሬው ዘመን ደግሞ የራሱን የቁርጥ ቀን ልጆች አፍርቷል፤ እርሱም "የመደመር ትውልድ" በሚል የጋራ መንፈስና ራዕይ የተጠመቁ የኢትዮጵያ ጽኑ ጠበቆች ናቸው።
የመደመር ትውልድ ማለት በዕድሜ ማዕቀፍ ብቻ የሚገደብ ስብስብ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ከፍታና ብልፅግና በልቡ ያነገበ፣ ለሀገሩ ክብር ቀናዒ የሆነ የነቃ አእምሮና የዳበረ ስብዕና ባለቤት ነው።
ይህ ትውልድ የኢትዮጵያ ጠበቃ ነው ስንል፣ በከንቱ ውዳሴ ወይም በስሜት መነዳት አይደለም። የመደመር ትውልድ ኢትዮጵያ ስትነካ የሚያንገበግበው፣ ስሟ በክፉ ሲነሳ የሚጎፈንነውና ክብሯ ሲደፈር የሚቆጣና የሚከፋው ቆራጥ ትውልድ ነው።
ሀገር ወዳድነት የመድረክ ላይ ዲስኩር ወይም የፖለቲካ መፈክር ሳይሆን፣ በደሙ ውስጥ የሚዘዋወር የሕይወት ትርጉም ነው። ኢትዮጵያን ዝቅ ለማድረግ የሚቃጣን ማንኛውንም የውስጥም ሆነ የውጭ ጥቃት በትዕግስትና በብልሃት፣ ካስፈለገም በማያወላውል ጀግንነት የሚመክት የዘመናችን የሀገር ጋሻ ነው። ለዚህ ትውልድ ኢትዮጵያ ማለት ከምንም ነገር በላይ የምትቀደም፣ ክብሯ የነፍሱ ክብር የሆነች፣ ማንም እንደፈለገ ሊዘፍንባት የማይፈቅድላት ውድ እናት ናት።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን ጂኦ-ፖለቲካዊና ታሪካዊ እጣ ፈንታ ለመቀየር የተነሳ የለውጥ ሐዋርያ ነው። አሁንም ደጅዋ የተዘጋባትን፣ ከተፈጥሮ ፀጋዋና ከውሃ የራቀችውን፣ በሴራ የየብስ እስረኛ እንድትሆን የተፈረደባትን ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ታሪካዊ መናገሻዋና የባህር አድማሷ ለመመለስ የቆረጠ ትውልድ ነው።
ይህ የባህር በርና የውሃ ጥያቄ ለእርሱ የቅንጦት ሳይሆን የህልውና፣ የፍትህና የትውልድ አደራ ጉዳይ ነው። የተዘጋውን ደጅ በሰላም፣ በዲፕሎማሲና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማስከፈት የሚጥር፣ ነገር ግን ለሀገሩ ታሪካዊ መብት ወደኋላ የማይል ብርቱ ጠበቃ ነው።