የከተሜነት እውነተኛ ትርጉም በሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች መደርደር ወይም በኮንክሪት ክምችት ብቻ ሳይሆን፣ ነዋሪዎች በክብር፣ በምቾትና በደህንነት በሚኖሩበት ዘመናዊ ሥርዓት ይለካል።
ካለፈው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እስከ 7ኛው ምርጫ ዋዜማ በተዘረጉት አምስት ዓመታት፣ የመደመር ትውልድ የከተሞቻችንን የትላንት ገፅታ በመቀየር፣ ከተሞችን ከድህነትና ከጥግግት አውጥቶ ለነዋሪዎቻቸው የተመቹ የብልፅግና ማዕከላት እንዲሆኑ አስደናቂ ስራዎችን በመንግሥት መሪነት አከናውኗል።
በእነዚህ የ5ቱ ዓመታት ገፆች ጎልቶ ከሚታየው ስኬት አንዱ የቤት ልማት አብዮት ነው። ቀደም ሲል ዘላቂና ውጤታማ ያልነበረውን የቤት ልማት ፕሮግራም በአዲስ መልክ በመቃኘት ታላቅ የቤት አቅርቦት ንቅናቄ ተደርጓል።
መንግሥት በዋነኝነት ሲያከናውነው የነበረውን ልማት ከግል ዘርፉ እንዲሁም ከመንግሥትና የግል አጋርነት (PPP) ጋር በማስተሳሰር የቤቶች ልማት በከፍተኛ ፍጥነት እንዲከናወን ተደርጓል። በዚህም ከ2013 እስከ 2017 በጀት ዓመት ባሉት ጊዜያት ብቻ ከመንግሥት፣ ከሪል ስቴት አልሚዎችና ከግል ቤት ሠሪዎች አቅም ጋር ተደምሮ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ቤቶች ተገንብተዋል። ከዚህ ጎን ለጎንም፣ ዐቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ቤት ፈላጊዎች በመንግሥት በኩል የሚከናወኑ የቤት ልማት ፕሮግራሞች ሳይቋረጡ ቀጥለዋል።
የመደመር ከተሜነት ሰውን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ፣ ማኅበረሰብን በማስተባበር ዐቅመ ደካማ ለሆኑ ወገኖች 166,207 ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች ተገንብተው ተላልፈዋል። ከተሞችን ከእርጅናና ከድህነት ገፅታ ለማላቀቅ፣ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ ሥራ በስፋት ተከናውኗል። በ2013 ዓ.ም ከ75 በመቶ በላይ የነበረውን ከደረጃ በታች የሆኑ (substandard) ቤቶች ድርሻ፣ በ2017 ዓ.ም ወደ 52 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል። ይህ ዜጎችን ከማይመችና ኋላቀር አኗኗር ወደ ዘመናዊ የኑሮ ሁኔታ በፈቃደኝነት ያሸጋገረ የክብር ጉዞ ነው።
ይህ ታላቅ የከተማ ትራንስፎርሜሽን የሲቪል ሰርቪሱንና የከተሞችን አገልግሎት ከማዘመን ጋር ተጣምሮ የተጓዘ ነው። ከተሞች ዘመኑን የዋጀ አደረጃጀትና የአስተዳደር ሥርዓት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶች ለዜጎች በተሻለ ቅልጥፍና እንዲቀርቡ ተደርጓል።
ይሁን እንጂ፣ መንግሥት ከተሞችን በተቀናጀ አግባብ ሲያለማ፣ አንዳንድ ኃይሎች ይህንን የልማት አቅጣጫ ባለመረዳት የተዛባ አመለካከት ሲያራምዱ ቆይተዋል። ዜጎችን ወደ ተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለማሸጋገር የሚሰሩትን የመልሶ ማልማት ስራዎች "ማፈናቀልና ማህበራዊ ኢንጂነሪንግ" ብለው ሲስሉ፣ የከተማን ይዞታ ስርዓት ለማስያዝና አረንጓዴ ቦታዎችን ለመጠበቅ የሚወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎችን በሌላ ስም ለማጠልሸት ሞክረዋል። አልፎ ተርፎም ከተሞቻችን ባህላችንንና ታሪካችንን እንዲያንፀባርቁ ለማድረግ የተሰሩትን የውበት ሥራዎች "ታሪክን እንደ ማውደም" አድርገው አቅርበዋል።
ሆኖም እውነታው በተግባር ሊደበቅ አይችልም። ዜጎቻችን የስራዎቹን ፋይዳ አውቀው ምስክርነታቸውን ሲሰጡ፣ የውጭ ሀገራት ሚዲያዎችና ዜጎች ሳይቀሩ በከተሞቻችን ላይ የተመዘገቡትን አስደናቂ ለውጦች እያደነቁ ይገኛሉ። የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የሲቪል ሰርቪሱን ውጤታማ ለማድረግ የሚከናወኑ ሪፎርሞችንም አሉታዊ ስም በመስጠት ለውጡን ለማደናቀፍ የተሞከሩ ሙከራዎች ከሽፈዋል። በአጠቃላይ እነዚህ የ5ቱ ዓመታት ገፆች፣ መንግሥት ከተሞችን የነገው ዘመን የሥልጣኔ ማዕከላት ለማድረግ ያለውን ግልጽ አቋምና የማድረግ አቅም በተግባር ያረጋገጡ፣ እንዲሁም ለነዋሪዎቻቸው ምቹና ዘመናዊ ከተሞችን የፈጠሩ ደማቅ ታሪካዊ ምዕራፎች ናቸው።