Search

"አስተሳሰብ ካልተቀየረ ለውጥ አይመጣም"- ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)

ረቡዕ ሰኔ 03, 2018 49

የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በኢቲቪ "ከበሻቱ ጋር" ፕሮግራም ላይ በቀረቡበት ወቅት፣ ከልጅነት ትዝታቸው ጀምሮ እስካሁን ስላላቸው የሙያ ፍልስፍና አስተማሪ ምስጢሮችን አጋርተዋል።

ሚኒስትሩ በቁምነገር የተሞላውን የስራ ህይወታቸውን ለጥቂት ሰዓታት ገታ አድርገው፣ በሳቅና በትዝታ የታጀበውን የህይወት ጉዟቸውን እንዲህ ተርከውታል።

ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ለውኃ ቴክኖሎጂ ሙያ ያላቸው ፍቅር በአጋጣሚ የመጣ አይደለም። ገና በአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን "ጣሪያው ላይ የሚወርደውን ዝናብ ለምን ወደ ቤት ውስጥ አንገድበውም?" በሚል የፈጠራ ሀሳብ ቤቱን በውኃ ሞልተውት እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ የልጅነት ድፍረትና ፍላጎት ዛሬ ለደረሱበት ትልቅ የሀላፊነት ቦታ መሰረት እንደሆነላቸው ይናገራሉ።

ትምህርት የጀመሩት ገና በለጋ እድሜያቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በአሬሬ ቱሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበራቸውን ት የልጅነት ቆይታ በማስታወስ፣  "በትምህርት ቤቱ ሰንደቅ ዓላማ እሰቅል ነበር፤ የኢትዮያን  ብሔራዊ መዝሙር እስከመጨረሻው ድረስ ከፍ አድርጌ የምዘምረው እኔ ነኝ" ይላሉ። ይህ የልጅነት ትጋታቸው እስከ ጀርመኑ ስቱትጋርት ዩኒቨርሲቲ ድረስ ዘልቆ ለፒ.ኤች.ዲ (PhD) ማዕረግ አብቅቷቸዋል።

ህይወታቸው የተቀረጸው በአርባ ምንጭ ከተማ እንደሆነ የሚናገሩት ኢንጅነር ሀብታሙ፤ በወጣትነት እድሜያቸው በከተማዋ በብስክሌት ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲጓዙ የነበረውን ትዝታ በናፍቆት አውስተዋል። አርባ ምንጭ ለእሳቸው የእውቀት ብቻ ሳይሆን፣ የሙያ መጀመሪያና የህይወት መማሪያ ትልቅ ትምህርት ቤታቸው ናት።

ወደ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመጡ ማግስት ካከናወኗቸው ስራዎች መካከል የሰራተኛውን አስተሳሰብ መቀየር ቀዳሚው ነበር። "ሰው የፈለገውን ያህል እውቀት ቢኖረው አስተሳሰቡ ካልተቀየረ ለውጥ አያመጣም" የሚሉት  ኢንጂነር ሀብታሙ (ዶ/ር) ፣ ሰራተኞቻቸው ለሰው ልጅ ያላቸው ክብርና አቀባበል እንዲቀየር ትልቅ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሚኒስትሩ ዛሬም ቢሆን ቢሯቸው ለማንኛውም ሰው ክፍት እንደሆነና በ"ፖዘቲቭ ኢነርጂ" ማመናቸው ለስራቸው ጉልበት እንደሆናቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ቢያሳስባቸውም፣ ዝናብን ግን ሁልጊዜም እንደ በረከት ነው የሚያዩት። "ዝናብ እርጥበት ነው፤ እርጥበት ደግሞ በረከት ነው" የሚሉት ሚኒስትሩ፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን በአግባቡ ማስተዳደር ከቻልን ዝናብ ለሀገራችን የብልጽግና ምንጭ መሆኑን በጽኑ ያምናሉ።

ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)  ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጎሬ ተነስተው የኢትዮጵያን ትልቅ ተቋም እስከመምራት የደረሱበት ጉዞ፣ ለብዙ ወጣቶች ተምሳሌት የሚሆንና "ካልታከተ መድረሻው ሩቅ አይደለም" የሚያሰኝ ነው።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ:

ተያያዥ ዜናዎች: