በመጋቢት እና ሚያዝያ 2018 ዓ.ም ወራት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳይንሳዊ የምርምር ልህቀት፣ በከተማ ልማት፣ በኢኮኖሚ ሪፎርም እና በቀጣናዊ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ያተኮሩ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ክንውኖችን አድርገዋል።
• የፕሮጀክቶች ምረቃ እና የሥራ ጅማሮ
የመጋቢት ወር በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተመረቁበት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (AHRI) ውስጥ ዘመናዊ የምርምር ማዕከል መርቀዋል። ይህ ማዕከል 40 የላብራቶሪ ክፍሎችን እና በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድኃኒቶችን ጥራት የሚያረጋግጥ የባዮ-ኢኩቫለንስ (bioequivalence) ማዕከልን ያካተተ ነው።
በከተማ ልማት ዘርፍ፣ የሚያዝያ ወር በአገልግሎት እና በዲጂታል መሠረተ-ልማት ግንባታ ረገድ ጉልህ እመርታ የታየበት ወር ነበር። የአራዳ ፓርክ ፕሮጀክት ከፍተኛ የሆነ የከተማ ገጽታ ለውጥ የታየበት ሲሆን፤ ቀደም ሲል ችላ ተብለውና ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩ ቤቶች የሚገኙበትን 40 ሄክታር መሬት ወደ ዘመናዊ ሁለገብ መዳረሻነት ቀይሮታል። ይህ የተቀናጀ የመሠረተ-ልማት እና የመሬት አጠቃቀም ውጤታማነት የታየበት ፕሮጀክት፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከ700 በላይ ነባር ቤቶችን የማደስ ስራን አካቷል። ከዚህም በተጨማሪ በ5.7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና የኦሊምፒክ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት መሠረተ-ልማቶችን፣ የ15 የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዎችን ሃውልት እና ለተነሺ ነዋሪዎች ተብለው የተገነቡ 105 የንግድ ሱቆችን የያዘው የአዲስ ስፖርት ፓርክ በዚሁ ወር ተመርቋል።
የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት አቅም ለማሳደግ የ100 ሜጋ ዋት የአሰላ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ተመርቋል። በተጨማሪም በሀዋሳ የቶዮ ምዕራፍ 2፣ የኦሪጂን እና የሉሚንቴክ የሶላር ፋብሪካዎች ሥራ ጀምረዋል። እነዚህ ፋብሪካዎች ከአዲሱ የኤች.ዜድ (HZ) ጋዝ ፋብሪካ ጋር በመሆን በዓመት 11.3 ጊጋ ዋት ንጹህ ኃይል ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በቱሪዝም ዘርፍ፦ በገበታ ለትውልድ መርሃ-ግብር የተገነባው የሀሮ ደንዲ ሎጅ በይፋ ተመርቋል። በመጨረሻም፣ እንደ መታወቂያ ምዝገባ እና የሥራ ፈቃድ ያሉ መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎቶችን በቀጥታ ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የታለመው የመሶብ ተንቀሳቃሽ የአውቶቡስ አገልግሎት ስራ ጀምሯል።
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአፍሪካ ኅብረት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና የዲጂታል ጤና መሪ ሆነው የተሾሙት በያዝነው የሚያዝያ ነው።
ይህ ኃላፊነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሉዓላዊነት፣ ለውጤታማነት እና ለአካታች ዕድገት ቁልፍ መሣሪያ የሆኑትን የፈጠራ ሥራዎችን እና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በማሳደግ ረገድ እያሳዩት ያለውን የአመራር ጥበብ እውቅና የሰጠ ሲሆን ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ንቁ አመራር ሰጪነት በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ያስመዘገበችውን ጉልህ ስራ የሚያሳይ ነው።
• የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የአፈጻጸም ግምገማ፦
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሦስተኛውን የ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም እና የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ግምገማ መርተዋል። በዚህም የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት 9.2 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ወደ 10.2 በመቶ እንደሚያድግ ይጠበቃል። ሪፖርቱ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ የተመዘገበውን ስኬታማ ሽግግር በዝርዝር ያሳየ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ኪሳራ ያስመዘግቡ የነበሩ ተቋማት በአሁኑ ወቅት 2.1 ትሪሊዮን ብር ገቢ ወደ ማስገባት ተሸጋግረዋል። ለዚህ ውጤት መገኘት ቁልፍ የሆነው የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገቱ ዋና መሪ እንዲሆን ቅድሚያ የሚሰጠው የሪፎርም አጀንዳ ነው። ይህም እንደ ካፒታል ገበያ ባሉ አዳዲስ የፋይናንስ ሥርዓቶች እና እያደገ በመጣው የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት እየተደገፈ ይገኛል።
• የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ፦
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማጠናከር አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን (AI) እና ሮቦቲክስን በመጠቀም ወደ ቺፕስ እና ዳታ (ኢንዱስትሪ 4.0) መሸጋገር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የውጭ ምርቶችን መተካት የቻለው “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የይዞታ መጠን ወደ 88 በመቶ ማድረሱን በስኬትነቱ ጠቅሰዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ ሰላማዊ የባሕር በር ማግኘት የሀገር የህልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት የሰጡ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳትሆን ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ወጪ እንደሚጨምርባት አስገንዝበዋል።
• ማህበራዊ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃ አመራር፦
“ማኅበራዊ ልማት እመርታ ለሀገር ግንባታ” በተሰኘው እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት የምክክር መድረክ ላይ፣ መንግሥት ባለፉት ስምንት ዓመታት ከ19.8 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን እና ይበልጥ ተዓማኒነት ያለው ሥርዓተ-ትምህርት ተግባራዊ መደረጉ ተገልጿል። በጤናው ዘርፍም በቅደመ መከላከል እና አክሞ ማዳን፤ መካከል የተሻለ ሚዛን ለመፍጠር ለ30 ዓመታት ያገለገለው ፖሊሲ እንዲሻሻል ተደርጓል። በአካባቢ ጥበቃ ረገድም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2027 የሚካሄደውን የኮፕ32 (COP32) ጉባኤን ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት የጀመረች ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዝግጅቱ ከሀገራዊው የአረንጓዴ ልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ መሆኑን እንዲያረጋግጥ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴውን ሰብስበው አቅጣጫ ተሰጥተዋል።
• ዲፕሎማሲ እና ቀጣናዊ ትስስር፦
ኢትዮጵያ የብሩንዲ፣ የላይቤሪያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንቶችን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያስተናገደች ሲሆን፤ ይህም በመከላከያ፣ በጤና፣ በትምህርት እና በዲጂታል መሠረተ-ልማት ዘርፎች ላይ ያተኮሩ በርካታ የመግባቢያ ስምምነቶች እንዲፈረሙ አስችሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአውሮፓ ህብረት ዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር፣ ከአፍሪካ ኤክስፖርትና ኢምፖርት (Afrexim) ባንክ ፕሬዝዳንት፣ እንዲሁም ከፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ እና የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጋር ተወያይተዋል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጅቡቲ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትርን በመቀበል በሁለትዮሽ ትብብሮች ዙሪያ የመከሩ ሲሆን፤ ከአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ጋር ደግሞ በአፍሪካ ህብረት ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና ዲጂታል ጤና ረገድ የተሰጣቸውን ሚና ጨምሮ ሰፋ ባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በሀገር ውስጥ ጉዳይ፦
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ከሆኑት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ጋር በመገናኘት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን የገመገሙ ሲሆን፣ የፕሬዝዳንቱን የሥራ ዘመን ለተጨማሪ አንድ ዓመት በይፋ አራዝመዋል።
የሚያዝ ወር የትንሳኤ በዓል የተከበረበት በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም በማዘጋጀትና አነስተኛ ገቢ ላላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሠራተኞች የቁሳቁስ ድጋፍ በማጋራት ተጠናቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት