Search

ከምኞት ወደ እውነት፦ የኢትዮጵያ አዲሱ የሉዓላዊነት ጉዞ በ21ኛው ክፍለ ዘመን

እሑድ ሚያዝያ 25, 2018 105

የኢትዮጵያ ታሪካዊ የሉዓላዊነት ጽንሰ-ሀሳብ በአብዛኛው የተገነባው ዜጎቿ ሀገርን ለማዳን በጦር ሜዳ ላይ በከፈሉት ወደርየለሽ መስዋዕትነት እና በፈሰሰው ደም ነው። ይህ አንጸባራቂ ታሪክ ኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት አድርጓታል። ይሁን እንጂ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እውነተኛ ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ከድንበር ጥበቃ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ እና አእምሯዊ ራስን መቻልን የሚጠይቅ ሁለንተናዊ ጽንሰ-ሀሳብ ሆኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ እንደሚያስገነዝቡት፣ አንዲት ሀገር ለምግብ፣ ለኃይል፣ ለዳታ መሰረተ ልማት ወይም ለዲፕሎማሲያዊ ትርክቶች በውጭ ኃይሎች ላይ ጥገኛ እስከሆነች ድረስ እውነተኛ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አትችልም። በመሆኑም አሁን ያለው ትውልድ ያንን በደም የተጠበቀ ነጻነት የተሟላ ለማድረግ እና ሀገራዊ ሕልውናን በጽኑ መሠረት ላይ በማቆም ከጥገኝነት ለመላቀቅ ወደ አዲስ ሁለንተናዊ የሽግግር ጉዞ ገብቷል።

ይህን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት ከማረጋገጥ አኳያ ቀዳሚው ምሰሶ ከምግብ ጥገኝነት መላቀቅ ነው። ለዓመታት ከምግብ ዋስትና እጦት እና ከእርዳታ ጋር ተያይዞ የነበረውን የሀገራችንን ገጽታ ለመቀየር ግብርናን ወደ ዘመናዊ እና ምርታማ ዘርፍ የማሸጋገር ሰፊ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለስንዴ ግዢ ታወጣ የነበረውን ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ በማስቀረት፣ በመስኖ ስንዴ ልማት ራሷን ችላ የውጭ ግዢን ሙሉ በሙሉ ማስቆም ችላለች። ከዚህም ባሻገር የ"ሌማት ትሩፋት" መርሐግብር የወተት፣ የዶሮ፣ የማር እና የእንቁላል ምርትን በማሳደግ የተመጣጠነ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ ነው። ይህን የግብርና ስኬት ዘላቂ ለማድረግ ደግሞ የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብርን በመተግበር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የሀገራችንን የደን ሽፋን ወደ 23.6 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል።

በኢንዱስትሪ እና በኃይል ልማት ራስን መቻል የዘመናዊ ሉዓላዊነት ሌላኛው አካል ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ማመንጨት ወደሚችለው ከ5 ሺህ ሜጋዋት በላይ ከፍተኛ አቅሙ ኢትዮጵያን ከኃይል እጥረት አላቅቆ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በሙሉ አቅም የሚያንቀሳቅስ አስተማማኝ መሠረት ይጥላል። በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የማምረት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እውን እየሆነ ነው። በዚህም እስከ 2018 በጀት ዓመት ዘጠነኛው ወር ድረስ ብቻ በተደረገ ርብርብ ምርት አቁመው የነበሩ 993 ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደርጓል። ይህም ሀገራችን በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያላትን አቅም አሟጥጣ እንድትጠቀም እና ከውጭ ጥገኝነት እንድትላቀቅ የሚያስችል ትልቅ ማሳያ ነው።

የነገዋን ኢትዮጵያ ለማጽናት ቴክኖሎጂያዊ ጥገኝነትን ማስቀረት የግድ ይላል። ለዚህም "የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ ሀገራዊ መረጃዎችን በሀገር ውስጥ ማዕከላት የማስተዳደር ሰፊ ሥራ እየተከናወነ ነው። የዲጂታል ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በኩል የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ42.6 ሚሊዮን በላይ መድረሱ ትልቅ ስኬት ነው። በሌላ በኩል የ"5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ ወጣቶችን በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በሶፍትዌር ማበልጸግ ክህሎት እያስታጠቀ ሲሆን፣ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ሥልጠናውን ማጠናቀቃቸው ለቴክኖሎጂ ሉዓላዊነታችን ጠንካራ የሰው ኃይል ግንብ እየተፈጠረ መሆኑን ያረጋግጣል።

እነዚህን ሁሉ ሀገራዊ ጥረቶች የሚያስተሳስረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ"እውነተኛ ሉዓላዊነት" ፍልስፍና ነው። የኢትዮጵያ ስፍራ አሁን ያለችበት አለመሆኑን፣ ቀጣዩ ትውልድ የተሟላ ሉዓላዊነቷን የተጎናጸፈች ሀገር እንዲረከብ የዛሬው ትውልድ ዋጋ መክፈል እንዳለበት በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተወሰዱ ያሉት ጥብቅ እርምጃዎችም ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ብቁ ትውልድ ለማፍራት እየከፈለችው ያለ የነገ ዋጋ ነው። ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ብሪክስ ፕላስን በመቀላቀል የራሷን ትርክት በራሷ በመጻፍ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የምታደርገው ጉዞ የዚሁ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት አካል ነው። በአጠቃላይ ይህ ጉዞ የሚያሳየው፣ በደም የተገኘውን የታሪክ ነጻነት በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ እና በአእምሮ በዳበረ የተሟላ ሉዓላዊነት ለማሸጋገር ኢትዮጵያ የተሳካ እና ታሪካዊ የትራንስፎርሜሽን ምዕራፍ ላይ መሆኗን ነው።

በለሚ ታደሰ