Search

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2026 የAPEX መንገደኞች ምርጫ 'በአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ' ሽልማትን አሸነፈ

ሰኞ ሚያዝያ 26, 2018 56

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2026 የAPEX መንገደኞች ምርጫ 'በአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ' (Best Airline in Africa) ሽልማትን በማሸነፍ የአቪዬሽን መሪነቱን አረጋገጠ።
ይህ እውቅና አየር መንገዱ በመላው ዓለም በሚያደርጋቸው በረራዎች ቀልጣፋ፣ ምቹ እና አስተማማኝ አገልግሎት ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፤ ሽልማቱም ሙሉ በሙሉ በመንገደኞች እውነተኛ የጉዞ ተሞክሮ እና ገለልተኛ አስተያየት ላይ የተመሰረተ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት፣ ሽልማቱ በዓለም ዙሪያ ያሉ የሠራተኞች የቡድን ሥራ ውጤት ሲሆን፤ ደንበኞች የሰጡት እውቅና አገልግሎቱን ይበልጥ ለማሻሻል ትልቅ መነሳሳት ይፈጥራል።
የAPEX ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጆ ሊደር (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተግባራዊ ቁርጠኝነቱ በአህጉሪቱና ከዚያም በላይ የአቪዬሽን መሪነቱን እያሳየ እንደሚገኝ መስክረዋል።
አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት በአምስት አህጉራት ከ160 በላይ መዳረሻዎች በዘመናዊ አውሮፕላኖች በረራ ያደርጋል።
የስታር አላይንስ አባል የሆነው ተቋሙ፣ ስካይትራክስን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ለተከታታይ ዓመታት ማሸነፍ ችሏል።
አየር መንገዱ 'ራዕይ 2040' በተሰኘው ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ በዓለም ካሉ 20 ቀዳሚ የአቪዬሽን ግሩፖች አንዱ ለመሆን እየሠራ ሲሆን፣ በቶጎ፣ ማላዊ፣ ዛምቢያ እና ኮንጎ ከሚገኙ አየር መንገዶች ጋር በመተባበር የበርካታ ማዕከላት (multi-hub) ስትራቴጂን በመተግበር ላይ ይገኛል።
በላሉ ኢታላ