ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ሀገራት ከተፈጥሮ ያገኙትን የማዕድን ሀብት በጥሬው ወደ ውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምረው ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ሲያውሉት ኢኮኖሚያቸው በከፍተኛ ፍጥነት ያድጋል። ይህ ዓይነቱ ስትራቴጂያዊ አሠራር የውጭ ምንዛሪን ከመታደግ እና ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ሀገራትን ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆ ሉዓላዊነታቸውን በኢኮኖሚ ያረጋገጡ ጠንካራ አምራች ያደርጋቸዋል።
በተፈጥሮ ሀብት የታደለችው ኢትዮጵያም ይህን እውነት በመገንዘብ የማዕድን ሀብቷን እሴት ጨምራ ወደ ተጨባጭ የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ለመቀየር ትልቅ ሪፎርም እያከናወነች ትገኛለች።
የማዕድንና ኢንዱስትሪ ትስስር ምንነት እና የሀገራት ተሞክሮ
የማዕድን እና ኢንዱስትሪ ትስስር (Mineral-Industrial Linkage) ውጤታማ የሚሆነው ከምድር የሚወጣን ማዕድን በጥሬው ከመሸጥ ይልቅ በሀገር ውስጥ በሚገኙ አምራች ፋብሪካዎች ውስጥ እንደ ግብዓት በመጠቀም እሴት መጨመር ሲቻል ነው።ለዚህም የአፍሪካ ተጠቃሽ ተሞክሮዎችን ማየት ይቻላል፡ ቦትስዋና በአልማዝ ማዕድን የበለፀገች ሀገር ነች። አልማዝን የመቁረጥ እና የማለስለስ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት ከዚህ ሀብቷ ተጠቃሚ በመሆን ከአፍሪካ ተጠቃሽ ነች። ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ ጠንካራ የማዕድን-ማኑፋክቸሪንግን ትስስር በመፍጠር ከማዕድኗ ተጠቃሚ ሆናለች። በተለይም ወርቅን እሴት በመጨመር ለገበያ በማቅረብ ረገድ በአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ነች።
አሁን ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው ፖሊሲም ማዕድናትን ወደ ኢንዱስትሪ በማስገባት ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለማምጣት እና ሕገወጥ ዝውውርን ለመግታት ያለመ ነው።
የትናንቱ ስብራት እና የሀገራዊ ሪፎርም አስፈላጊነት
ከሪፎርሙ በፊት የነበረው የማዕድን ፖሊሲ ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት አናሳ ከመሆኑም በላይ አሠራሩ በጥሬ ዕቃ ላኪነት ላይ የተገደበ ነበር። በዚህም ምክንያት ዘርፉ ለጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) የሚያደርገው አስተዋጽኦ ከአንድ በመቶ በታች ሆኖ መቆየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በወቅቱ የማዕድን ሀብቱ ለሀገር ልማት ከመዋል ይልቅ፣ ከግልጽነትና ተጠያቂነት በራቀ አሠራር ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የተጋለጠ ሆኖ መቆየቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
እንደ ወርቅ ባሉ ውድ ማዕድናት ላይ የነበረው የምርት እና የግብይት ሰንሰለት በሙስና የተተበተበ እንዲሆን በማድረግ፣ ሀገራችን ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ እንድታጣ ሲደረግ ቆይቷል። በዘርፉ ላይ ከነበረው ሥር የሰደደ ሌብነት የተነሳ፣ 'ባሌስትራ' ወርቅ ነው ተብሎ ለብሔራዊ ባንክ እስከመቅረብ የደረሰበት አሳፋሪ ታሪክ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የማዕድን ፍለጋ እና ልማት ሥራዎችም ግልጽ የሆነ ሀገራዊ ፋይዳ ባለው መልኩ አይመሩም ነበር።
ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ማዕድንን የኢኮኖሚው ዋነኛ ምሰሶ በማድረግ የኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረት አድርጎታል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያና ለብረት ግብዓቶች ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ ከጥሬ ማዕድን ሽያጭ ወደ እሴት ጭማሪ የተደረገው ሽግግር ወሳኝ እርምጃ ነው።
ተስፋ ሰጪው የብረት እና የግንባታ ግብዓቶች ምርት ጅማሮ
ሀገራችን ያላትን ከ1.1 ቢሊዮን ቶን በላይ የብረት ማዕድን ክምችት ወደ ተጨባጭ ሀብት ለመቀየር በዓመት ሦስት ሚሊዮን ቶን ብረት በሀገር ውስጥ ለማምረት ግብ ተቀምጦ እየተሠራ ይገኛል። በዚህ ረገድ የብረት ማዕድን ፍለጋውን ያጠናቀቀው ዜድ ዋይ ቲ ቢ ዲ አይ ኤም (ZYTB DIM) ኩባንያ ወደ ማምረት እንዲሸጋገር ፈቃድ ማግኘቱ ትልቅ እመርታ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በሴራሚክ እና እብነ በረድ ምርቶች ላይ የታየው መነቃቃት የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ያፋጠነው ሲሆን፣ በዚህ ዓመት የሀገራችንን የሴራሚክ ፍላጎት 70 በመቶ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ዕቅድ ተይዟል። ዲዩአን ሴራሚክ ብቻውን በአመት 28 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምርት በመተካት ላይ ይገኛል።
የወርቅ ምርት ስኬት እና የውጭ ምንዛሪ ግኝት
ባለፉት ዓመታት በወርቅ ምርት ዘርፍ የታየው ውጤትም ሌላው የሪፎርሙ ስኬት ማሳያ ሲሆን፣ ለኤክስፖርት የቀረበው የወርቅ ምርት ከ2010 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት የ1241.4 በመቶ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። አምራቾች ምርታቸውን በቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ የተደረገው ማበረታቻ ኮንትሮባንድን በመቀነስ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን አሳድጎታል።
የዋይ ኤም ጂ ማዕድን፣ የኢትኖ ማዕድን እና ኢዛና ማዕድን ያሉ የወርቅ ማዕድን ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ገብተዋል። በቀጣይም እንደ ቱሉ ካፒ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ወደ ሙሉ ምርት ሲገቡ የወርቅ ምርት አቅም በከፍተኛ ደረጃ የሚጨምሩ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ወርቅን አጣርታ እሴት ጨምራ ለገበያ የምታቀርብበትን ፋብሪካ በቅርቡ ለአገልግሎት ለማብቃት እየሠራች ሲሆን፣ የዚህ ፋብሪካ ትርጉም ወርቅ ከማምረት በላይ ነው። ፋብሪካው ጥራት ያለውን ወርቅ በማምረት እሴት ጨምሮ ለገበያ የሚያቀርብ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሆነ ፕሮጀክት ነው።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እና የቀጣይ የልማት ዕቅድ
የማዕድን እና የኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጠናከር "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የጎላ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በዚህ ንቅናቄ አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብዓታቸውን ከሀገር ውስጥ ማዕድናት እንዲያገኙ በመደረጉ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 4.85 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል።
በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ የማዕድን ዘርፉን ለሀገራዊ ምርት (GDP) ያለውን አስተዋጽኦ ወደ 14 በመቶ ለማሳደግ ታቅዶ እየተሠራ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን መሆኑ በተጨባጭ ውጤቶች እየተረጋገጠ ይገኛል።
በለሚ ታደሰ