Search

የሚዲያ ዘርፉ እውነትን በማሳወቅ እና ለጋራ ብሔራዊ ማንነት ግንባታ በትኩረት ሊሠራ ይገባል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ዓርብ ሚያዝያ 30, 2018 57

መንግሥት የሚዲያ ምህዳሩ በነጻነት እንዲሠራ የሚያስችለውን ምቹ አውድ መፍጠሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ዘርፉ የታዩ ድክመቶችን በማረም ለጋራ ብሔራዊ ማንነት ግንባታ በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል።
ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የጠንካራ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሚዲያው በዚህ ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።
ከለውጡ በፊት ለመናገር እና ለመጻፍ እንቅፋት የነበሩ አሳሪ ሕጎች፣ በተለይም የፀረ-ሽብር ሕጉ በሚዲያ ነጻነት ላይ የነበረው ተጽዕኖ እንዲሻሻል መደረጉንም አስታውሰዋል።
በሚዲያ ነጻነት ዙሪያ በርካታ መሠረታዊ ለውጦች መከናወናቸውን ገልጸው፣ በሙያቸውና በዘገባዎቻቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች እንዲፈቱ መደረጉን አንስተዋል።
በተጨማሪም ከውጭ በሚተላለፉ የሚዲያ ስርጭቶች ላይ ይደረግ የነበረው የሲግናል ማፈን እንዲቆም መደረጉንና ታግደው የነበሩ የውጭ ሚዲያዎችና ጋዜጠኞች በነጻነት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሠሩ መፈቀዱን ገልጸዋል።
ሆኖም የሚዲያ ምህዳሩን የማስፋቱ ሂደት ያለ ፈተና እንዳልነበረ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ያልተከተሉና የተሰጠውን ነጻነት በአግባቡ መጠቀም የተሳናቸው አካላት መኖራቸው በሂደቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉን ጠቁመዋል።
በመሆኑም የሚዲያ ተቋማት እውነትን በማሳወቅና የጋራ ብሔራዊ ማንነትን በመገንባት ረገድ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ:

ተያያዥ ዜናዎች: