Search

የነዋሪዎቻችንን የኑሮ ጫና ለመቀነስ 18 ቢሊዮን ብር ደጉመናል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ዓርብ ሚያዝያ 30, 2018 56

በዛሬው ዕለት በተካሄደው 3ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመራጭና ተመራጭ እንዲሁም ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ አቅርበዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ ከቤት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም 5 ስትራቴጂዎች ተነድፈው በመንግሥት በጀት፣ በመንግሥትና በግል አጋርነት፣ በግል፣ በሪል ስቴት እና በግለሰብና ግለሰብ ቤቶች እየተገነቡ ይገኛሉ ብለዋል።
በዚህ በጀት ዓመት በመንግሥት በጀት 50 ሺህ፣ በመንግሥትና የግል አጋርነት 55 ሺህ በአጠቃላይ 105 ሺህ ቤቶች እየተገነቡ መሆኑንና አፈጻጸማቸውም ከ40 እስከ 90 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል። በመንግሥት የሚገነቡት ሲጠናቀቁ ቅድሚያ ተሰጥቶ እየቆጠቡ ላሉት እንደሚተላለፉም አረጋግጠዋል።
የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ከንቲባዋ ሲያስረዱ፣ ክስተቱ ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም በገበያ ማዛባት እንዳይባባስ የቁጥጥር ሥርዓት ተዘርግቷል ብለዋል።
የምርት አቅርቦትን ለማሳደግ፣ በአምስት መግቢያ በሮች ስድስት የገበያ ማዕከላትንና የእሁድ ገበያዎችን በመመስረት ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በልዩ ልዩ ዘርፎች ላይ 18 ቢሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ የነዋሪዎችን ጫና ለመቀነስ መሠራቱን ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ 4 አዳዲስ ሆስፒታሎችና 9 በመጀመሪያ ሆስፒታል ደረጃ የተገነቡ ጤና ጣቢያዎች መገንባታቸውን ከንቲባዋ ጠቁመዋል።
ነባር ሆስፒታሎችም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲሟላላቸውና የአልጋ ቁጥራቸው በእጥፍ እንዲጨምር ተደርጎ መታደሳቸውን አብራርተዋል።
የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል የመንገድ መሠረተ ልማትን የማስፋት ሥራ መሠራቱን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ የመንገድ ሽፋን ከ12.8 በመቶ ወደ 20 በመቶ ማደጉንና 163 ሺህ መኪናዎችን ማቆም የሚችሉ ፓርኪንጎች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
ለሕፃናት ምቹ የሆኑ ከ5 ሺህ በላይ መጫወቻዎችና ከ1 ሺህ በላይ የዴይ ኬር ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አመልክተዋል።
ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያዎችና ስታዲየሞች እየተገነቡ መሆኑን እንዲሁም 3 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች ልዩ ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን ከንቲባዋ ገልጸዋል። ከነጠላ ትርክት ይልቅ አሰባሳቢ ትርክትን ለመፍጠር የኪነጥበብ መከወኛዎች መገንባታቸውንም አክለዋል።
የከተማዋን ጎስቋላ ገጽታ ለመቀየር በተሠራው ሥራ 74 በመቶ የነበረውን ወደ 30 በመቶ ማድረስ መቻሉንና በቀጣይ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ዕውቅና መገኘቱን ከንቲባዋ አስታውቀዋል።
የከተማ መብራትን በማስፋፋት ረገድም ጨለማ የነበሩ አካባቢዎች በመቃጠላቸው የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መቀነሱን ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል "የአዲስ መሶብ" አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በስድስት ማዕከላት ተግባራዊ መደረጉንና 150 አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ እየተሰጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሙስናንና እጅ መንሻን በተመለከተም እስካሁን 420 ተጠርጣሪዎች (40 አመራር፣ 230 ባለሙያ እና 150 ተጠቃሚዎች) በቁጥጥር ስር ውለው እንደየተሳትፏቸው ተጠያቂ መደረጋቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማብራሪያቸው አረጋግጠዋል።