ሚዲያ እና ብሔራዊ ጥቅም
ሚዲያ የሀገርን ዳር ድንበር እና ሉዓላዊነት ከሚጠብቀው የመከላከያ ሠራዊት ባልተናነሰ፣ የሕዝብን ሥነ-ልቦናዊ እና ትርክት ሉዓላዊነት የመጠበቅ ታላቅ ኃላፊነት አለበት።
ለአብነት ያህል፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ የባሕር በር እና አጠቃላይ ፍላጎት በተመለከተ ሚዲያዎች ጉዳዩን ከቀጣናዊ ፉክክር ወይም ከጦርነት አጀንዳነት አውጥተው፣ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሕልውና፣ ከኢኮኖሚያዊ ፍትሕ እና ከታሪካዊ መብት አንጻር በመቅረጽ የሀገራችንን ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሞራል ልዕልና እንዲቀበሉት የማድረግ አቋም ሊይዙ ይገባል።
ከዚህ ባለፈ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሀገራት ኅብረ ብሔራዊ ትርክትን በማጉላት የሀገርን አንድነት የማጽናት የሞራል ግዴታም ኃላፊነትም አለባቸው።
የሚዲያ ሪፎርም ጉዞ እና የነፃነት አስተዳደር ፈተናዎች
ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት ያካሄደችው የሚዲያ ዘርፍ ሪፎርም የመገናኛ ብዙኃን ምሕዳሩን ከመሠረቱ የቀየረ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተስፋ የፈነጠቀ እርምጃ ነው። የሪፎርሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ በሙያቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችን እና ብሎገሮችን በመፍታት፣ በስደት የነበሩ እና ይታገዱ የነበሩ የሳተላይት እና የድረ-ገጽ ሚዲያዎችን ወደ ሀገር በማስገባት እንዲሁም የሚዲያ አፈናን ሕጋዊ ሽፋን ይሰጡ የነበሩ የጸረ-ሽብር እና የሚዲያ ሕጎችን በማሻሻል የታጀበ ነበር።
ሆኖም ይህ የተከፈተው የነፃነት በር ከባድ ፈተናዎችንም ይዞ መጥቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ነፃነትን በጥቁር ማስተዳደር" በማለት የገለጹት ፈተና፣ በዘርፉ በቂ ዕውቀት እና የሙያ ሥነ-ምግባር ሳይኖራቸው ወደ ኢንዱስትሪው የገቡ አካላት ሚዲያውን ለዋልታ ረገጥ ትረካዎች እና ለብሔራዊ አንድነት ጠንቅ ለሆኑ አጀንዳዎች መጠቀማቸው ዋነኛው ፈተና ነው።
አሁናዊው የሚዲያ ምኅዳር በነፃነት እና በኃላፊነት መካከል ያለውን ሚዛን የመጠበቅ፣ ከጥሬ መረጃ ወደ ጥልቅ ዕውቀት የመሸጋገር እና ከአክቲቪዝም በጸዳ መልኩ ለሀገራዊ ኅልውና የመቆም ታላቅ የቤት ሥራ አለበት።
ታዋቂው የሚዲያ ምሁር ዴኒስ ማክዊል በማኅበራዊ ኃላፊነት ፅንሰ-ሐሳባቸው እንዳሰፈሩት፣ የሚዲያ ነፃነት ከኃላፊነት ጋር ካልተጓዘ ሀገራዊ አደጋ መጋበዙ አይቀሬ ነው።
የመንግሥት ፍላጎት እና የተግባር ንጽጽር በሚዲያ ነፃነት ዙሪያ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እሳቤ እና ተግባር ስናነፃጽር ይህንን ሚዛን የመጠበቅ ፈተና በግልጽ እናየዋለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በርን ስንከፍት ንፁህ አየር ብቻ ሳይሆን አቧራም ይገባል፤ ነገር ግን አቧራ ገባ ብለን በሩን አንዘጋም" በማለት የሚዲያ ነፃነት መርሕን አጽንተዋል።
ይህ እሳቤ በተግባር ሲተረጎም፣ በአንድ በኩል አዲሱን የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/2013ን በማፅደቅ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት በመቀነስ ነፃነትን አስፍተዋል። በሌላ በኩል "አቧራ" ያሉት የጥላቻ ንግግር እና የብሔር ግጭት ቀስቃሽ ትርክቶች ሲበራከቱ ደግሞ፣ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣ አዋጅ ቁጥር 1185/2012 በማጽደቅ ማዕቀፍ ተበጅቷል። ይህ የሚያሳየው ሀገረ መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ትርክቶችን የመቆጣጠር ፈተና ምን ያህል ከባድ መሆኑን፣ ነገር ግን መከላከል ደግሞ ግዴታ መሆኑን ነው።
የሀገረ መንግሥት ግንባታ አቅም እና የአሰባሳቢ ትርክት ውስንነቶች
መገናኛ ብዙኃን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ዋነኛ መሣሪያዎች ቢሆኑም፣ በኢትዮጵያ ያሉት የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎች አሰባሳቢ ትርክትን በመፍጠር ረገድ መሠረታዊ ውስንነቶች ይታዩባቸዋል።
የመንግሥት ሚዲያዎች አልፎ አልፎ የዕለታዊ የፖለቲካ አስተዳደሩን አጀንዳዎች ከመዘገብ አልፈው፣ ዘላቂ እና ሁሉንም ዜጋ የሚያስማሙ የሀገረ መንግሥት ምሰሶዎችን በማጽናት ረገድ ክፍተት ይስተዋልባቸዋል።
በሌላ በኩል የግል እና የማኅበረሰብ ሚዲያዎች ብዙ ጊዜ በብሔር ማንነት ወይም በቡድን ፍላጎት ላይ ያተኮሩ ትርክቶችን በማስቀደም የጋራ ማንነትን የሚሸረሽሩ ተግባራት ላይ ሲሰማሩ ይታያል። በሀገር በቀል ጥናቶች፣ ለምሳሌ በፕሮፌሰር ዮሐንስ ምትኩ እና በዶ/ር ነገሪ ሌንጮ እንደተመላከተው፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ ከብሔር ፖለቲካ ጋር ያለው ቁርኝት አሰባሳቢ ትርክትን ከመገንባት ይልቅ ልዩነትን ለማስፋት ሲውል ቆይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ የጠቅላይነት ባሕሪ የሚታይባቸው ሚዲያዎች ደግሞ አካታችነትን ከግምት ባለማስገባት ለሀገር ፈተና ሲሆኑ ይታያል።
ሚዲያ በባሕርይው "ባለ ሁለት ስለት ጎራዴ" በመሆኑ፣ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መረጃ በማቅረብ ግጭቶችን መፍታት የሚችልበትን አቅም ትቶ የልዩነት እና የጥርጣሬ ዘር መዝራት ውስጥ ከገባ ሀገረ መንግሥቱን የማዳከም አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል።
አሰባሳቢ ትርክትን ለመፍጠር የሚዲያ ተቋማት ከጥላቻ ንግግር እና ከሴራ ትንታኔ በመውጣት፣ በምርምር እና በጥናት የተደገፉ እንዲሁም የሀገርን የረጅም ጊዜ ጥቅም የሚያስከብሩ ገዢ ትርክቶችን የማመንጨት ኃላፊነት አለባቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ፣ መደበኛው ሚዲያ (Mainstream Media) ብቻ ሳይሆን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አልጎሪዝሞች ፅንፈኝነትን በማራገብ ረገድ ያላቸውን ተፅዕኖ መረዳት እና ኅብረተሰቡ የሐሰተኛ መረጃዎችን እንዲለይ የማኅበረሰብ የሚዲያ ንቃት ማጎልበት ያሻል።
የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ትምህርት፦ ብሔራዊ ጥቅም እንደ መመሪያ
በዓለም አቀፍ ደረጃ በዴሞክራሲያዊነታቸው የሚታወቁ ሀገራት ሚዲያዎች እንኳን ከሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም አንጻር የማይደራደሩባቸው ጉዳዮች መኖራቸው ለኢትዮጵያ ሚዲያዎች ትልቅ ትምህርት ይሰጣል። ለአብነት ያህል፣ የአሜሪካ ዋና ዋና ሚዲያዎች ዓለም አቀፍ ክስተቶችን የሚዘግቡት ከአሜሪካ ስልታዊ ጥቅም አንጻር መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
ኤድዋርድ ኸርማን እና ኖአም ቾምስኪ "Manufacturing Consent" በተሰኘው ጥናታቸው እንዳረጋገጡት፣ ሚዲያዎች ሁልጊዜም የሀገራቸውን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አጀንዳ ያራምዳሉ። በተለይም ከሀገራቸው አንጻር ተፎካካሪዎች ናቸው የሚሏቸውን ሀገራት እንደ ተቀናቃኝ የሚፈርጁ ትረካዎችን በማቅረብ የሕዝባቸውን አመለካከት ይቀርጻሉ። ይህን ለማድረግ ደግሞ እንደ ዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት ያሉ ጉዳዮችን እንደ ሽፋን ይጠቀማሉ።
የእንግሊዙ ቢቢሲ ምንም እንኳን ገለልተኛ እንደሆነ ቢነገርለትም እንደ ኢራቅ ጦርነት ባሉ የሀገሪቱ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ የመንግሥትን ምንጮች በስፋት በመጠቀም የሀገሪቱን ስልታዊ አቋም የማንጸባረቅ ዝንባሌ አሳይቷል።
የግብፅ ሚዲያዎች በበኩላቸው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጉዳይ "የሕልውና ስጋት" አድርገው በመሳል፣ መላው የግብፅ ሕዝብ በአንድ አቋም እንዲቆም እና መንግሥታቸውን እንዲደግፍ የማድረግ ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ይሠራሉ። እንደ አልጀዚራ ያሉ የመካከለኛው ምሥራቅ ሚዲያዎችም የኳታርን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ ተከትለው ትርክትን እንደሚቀርጹ ይታወቃል።
በእነዚህ የተጠቀሱ ሀገራት ዜጎች በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የተከፈቱ ሚዲያዎች ከሀገራቸው መንግሥታት ጋር ምንም ያክል ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገራቸው ብሔራዊ ጥቅም ላይ ሁሌም ከመንግሥታቸው ጎን ናቸው።
ለዚህ ደግሞ በሀገራቸው እንዳይኖሩ የተከለከሉ ግብፃውያን የሚመሩት ሚዲያዎች እንኳን በግብፅ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያላቸውን አቋም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ በሚያራምዱት አመለካከት ማየት በቂ ነው።
እነዚህ ተሞክሮዎች የሚያሳዩት፣ ሚዲያ በውስጥ ጉዳይ ላይ መንግሥትን ቢተችም እንኳን በሀገር ኅልውና እና በብሔራዊ ጥቅም ላይ ግን "ገለልተኛ" መሆን እንደሌለበት እና እንደማይችልም ነው።
የኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ አስተሳሳሪ ትርክት እና የሚዲያ ድርሻ
ኢትዮጵያ 76 ቋንቋዎችና ብዝኃ ማንነት ያላት ሀገር ነች። ሚዲያው ይህንን ብዝኃነት እንደ ውበትና እንደ ጥንካሬ የሚጠቀም አስተሳሳሪ ትርክት የመገንባት ግዴታ አለበት። የሚዲያው ድርሻ ጠባብ የብሔርተኝነት እንዲሁም ጠቅላይ እና ጨፍላቂ ትርክቶችን ማስተጋባት ሳይሆን፣ በጋራ ታሪክ፣ በጋራ ግቦችና በጋራ እጣ-ፈንታ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው። ይህን ለማሳካት ሚዲያዎች ከስሜታዊነት ይልቅ ለዕውቀትና ለምርምር ቅድሚያ በመስጠት ትክክለኛውን ትርክት መፍጠር ይኖርባቸዋል።
አስተሣሣሪ ትርክት ማለት ልዩነቶችን ማጥፋት ሳይሆን፣ ልዩነቶች የሚከበሩበት እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ራሱን የሚያይበት የጋራ ቤት የመገንባት ጥበብ ነው። ሚዲያዎች እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የባሕር በር እና የምግብ ዋስትና ባሉ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የዜጎችን ተስፋ የሚያለመልሙ እና አንድነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በውስጥ አከራካሪ ጉዳዮች በምክክር እና በሐሳብ ፍጭት እንዲፈቱ የማድረግ ኃላፊነትም የሚዲያዎች ነው።
በውጭ ጉዳይም ቢሆን ሚዲያዎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም ኃላፊነታቸው ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውም ጭምር ነው። የአሜሪካ ሚዲያዎች የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና የአሜሪካን ታላቅነት በዓለም ዜጎች ሁሉ አዕምሮ ውስጥ ለመሳል የሚደክሙት በዚህ መርሕ ነው።
ሀገረ መንግሥትን ከሥርዓተ መንግሥት የመለየት ውስንነት እና መፍትሔው
በኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳር ውስጥ ያለው ትልቁ ውስንነት ሀገረ መንግሥትን ከሥርዓተ መንግሥት ለይቶ አለማየት ነው። ብዙ ጊዜ የሚዲያ ተቋማት ሥርዓተ መንግሥቱን ወይም ገዢውን ፓርቲ ሲቃወሙ ሀገረ መንግሥቱን የሚጎዱ ትረካዎችን ሲያራምዱ፣ ወይም መንግሥትን ሲደግፉ የሀገረ መንግሥቱን ዘላቂ ጥቅም ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ጋር ሲቀላቅሉ ይታያሉ። ይህንን ክፍተት ለመሙላት የሚዲያ ተቋማት በሕግ የተጠበቀ ኤዲቶሪያል ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል። ይህም መንግሥትን በኃላፊነት እንዲተቹ ነገር ግን ለሀገር ሕልውና በጽናት እንዲቆሙ ያስችላቸዋል።
መፍትሔው ጋዜጠኞች ከግል እና ከፓርቲ ጥቅም ገለልተኛ ሆነው፣ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም ግን ወጋኝ እንዲሆኑ የሚያስችል የሙያ ደረጃ መገንባት ነው። የመንግሥት ሚዲያዎች ወደ ሕዝብ አገልግሎት ሚዲያ በማደግ የሕዝብን ድምፅ እና የሀገርን ሕልውና ማዕከል ማድረግ፣ የግል ሚዲያዎችም ከአክቲቪዝም ወደ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት በመሸጋገር የሀገር ግንባታ ምሰሶ መሆን ይኖርባቸዋል።
ሚዲያው የመንግሥት ባለሥልጣናትን አፈጻጸም በጥብቅ እየተቆጣጠረ፣ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የሕዝብን የጋራ ደኅንነት ግን እንደ ቅዱስ ተግባር ሊጠብቅ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ከሚዲያ አመራር ጀምሮ እስከ ጀማሪ ሪፖርተር ያለው የሚዲያ ማኅበረሰብ የጋራ አቋም ሊይዝ ይገባል።
የሰላም ጋዜጠኝነት እና የብሔራዊ ጥቅም ዘብነት
የሚዲያ ተቋማት ሀገረ መንግሥቱን ጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ‘ከችግር ፈጣሪነት ወደ መፍትሔ አመንጪነት' መሸጋገር አለባቸው። በሀገር ውስጥ በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች እና ግጭቶች ወቅት፣ ሚዲያው የሞቱ ሰዎችን ቁጥር እና የጥፋት መጠን በማጉላት የልዩነትን ግድግዳ ከማስፋት ይልቅ፣ 'የሰላም ጋዜጠኝነት' መርሕን በመከተል የተጎዱ ማኅበረሰቦችን ሰብዓዊነት፣ የሰላም ጥሪዎችን እና የባሕላዊ ዕርቅ ሥርዓቶችን በማጉላት አቋም መውሰድ አለበት።
ብሔራዊ ጥቅም ማለት የጦር መሣሪያ ድል ብቻ ሳይሆን፣ የማይፈርስ የሕዝብ አንድነት እና የጋራ ሥነ-ልቦና መገንባት ጭምር በመሆኑ ሚዲያው የዚህ ቅዱስ ዓላማ ጠባቂ ሆኖ ሊዘልቅ ይገባል።
በለሚ ታደሰ