Search

ኢትዮጵያ የሁሉንም ዘርፎች መረጃ በአንድ ቋት የሚያስተናግድ 'ናሽናል ክላውድ' በቅርቡ ይኖራታል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ግንቦት 01, 2018 81

ኢትዮጵያ በተበታተነ መልኩ የሚገኙ የመንግሥት እና የግል ተቋማት መረጃዎችን በአንድ ማዕከል የሚያገናኝ ግዙፍ 'ናሽናል ክላውድ' (ብሔራዊ የመረጃ ቋት) የመገንባት ሥራ እየከናወነች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ይህ ብሔራዊ የመረጃ ቋት በቀጣዮቹ 18 ወራት እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት እንደ ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)፣ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና ኢትዮ-ቴሌኮም ያሉ ተቋማት የየራሳቸው የመረጃ ቋት እና የዲጂታይዜሽን ሥራዎች ቢኖራቸውም፣ ከመረጃ ቋት ባለፈ ግን "ናሽናል ክላውድ" ያስፈልገናል ነው ያሉት።

"የመረጃ ቋት ወይም ‘ዴታ ቤዝ’ በየተቋማቱ አለ፤ ነገር ግን እኛ የምንፈልገው ከዚያ ያለፈ ትልቅ ነገር የሆነውን ናሽናል ክላውድ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም ግብርናውን፣ ንግዱን እና ሚዲያውን ጨምሮ የሁሉንም ኢትዮጵያውያን መረጃ በአንድ ላይ አቀናጅቶ የሚይዝ እንደሚሆን አስረድተዋል።

በመረጃ አያያዝ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች በወደፊት ትውልድ ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን ተፅዕኖ ሲያብራሩ፣ "ወርቅ እና ብር እየጠበቅን፣ ውኃን እናስተዳድር እያልን ዳታን በአግባቡ ማስተዳደር ካልቻልን ሄዶ ሄዶ ልጆቻችን ይቸገራሉ" ብለዋል።

ይህን ስጋት ለመቅረፍም በ"ዲጂታል 2030" ስትራቴጂ ውስጥ ለመረጃ ቋት ግንባታው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በማብራሪያቸው ወቅት መረጃን ከማከማቸት ባለፈ፣ መረጃን ተደራሽ የማድረግ ችግር እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አልሸሸጉም።

ለአብነትም መረጃን ፊት ለፊት ተቀምጦ በጥያቄ እና መልስ ብቻ ለማግኘት የሚሹ፣ ዘመኑ በትዊተር እና በፌስቡክ መቀየሩን ያልተረዱ አካላት መኖራቸውን አንሥተዋል።

በሌላ በኩል አንዳንድ ሚዲያዎች የአንድን ሚኒስትር የግል ሕይወት፣ የአለባበስ እና የቢሮ ሁኔታ ለማሳየት አቅም እያላቸው፣ ስለ ዋናው የሥራ ክንውን መረጃ ለማግኘት መቸገራቸው ጥያቄ የሚያስነሣ መሆኑንም ገልጸዋል።

መረጃን ለሥራ ከመጠቀም ይልቅ በፕሮፌሽናሊዝም እጥረት ምክንያት በሌሎች ፍላጎቶች የመመራት ዝንባሌዎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ይህም ሊፈተሽ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የመቶ ዓመታት የመንግሥታት ታሪክ፣ እንዲሁም በኢቢሲ የብዙ ዘመናት የ‘ሃርድ ኮፒ’ ሰነዶች ወደ ዲጂታል የተቀየሩ ቢሆንም፣ በቀጣይ የሚገነባው "ናሽናል ክላውድ" እነዚህን ሁሉ መረጃዎች በአንድ ማዕከል በማገናኘት ለሀገራችን ዲጂታል ሽግግር ትልቅ መሠረት እንደሚሆን ይጠበቃል።

በዮናስ በድሉ