Search

የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የሰውነት እሴትን የሚያጎለብት ታላቅ ኃይል ነው፡- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

እሑድ ግንቦት 02, 2018 47

"የሕዝቦች ሰላምና አብሮነት ለጋራ ብልጽግና" በሚል መሪ ቃል የሕዝብ ለሕዝብ የሰላምና የአብሮነት ኮንፈረንስ በታሪካዊቷ የሐረር ከተማ በድምቀት ተካሂዷል።
የሐረሪ እና የኦሮሞ ሕዝቦችን ለዘመናት የዘለቀ ጠንካራ የአብሮነት እሴት ይበልጥ ለማጎልበት ያለመው ይህ መድረክ፣ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት የሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል።
በመድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ፣ ሰላም ለአንድ ሀገር ዕድገት፣ ለዜጎች ደህንነትና ለነገ ተስፋ መሠረት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣ ሰላም ማለት የጦርነትና የግጭት አለመኖር ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ መከባበር፣ መደማመጥ እና ልዩነቶችን በውይይት መፍታት መቻል ጭምር ነው።
ልዩነቶቻችን የመከፋፈል ምክንያት ሳይሆኑ ይልቁንም የመቀራረብ ኃይል መሆን እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ኦርዲን፣ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የሰውነት እሴትን የሚያጎለብት ታላቅ ኃይል መሆኑን አስገንዝበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም የሐረሪ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ለዘመናት በአንድ ገበያ የተገበያዩ፣ በአንድ ሰፈር የኖሩ፣ በደስታ ተሳስበው በችግርም የተደጋገፉ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ግንኙነታቸው በታሪክ፣ በደም እና በላብ የተገነባ ጠንካራ መሠረት እንዳለው አብራርተዋል።
በመድረኩ ከሐረሪ ክልል፣ ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን እና ማያ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በቴዎድሮስ ታደሰ