በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ልዩነቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ታላቅ ተስፋ የተጣለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ በአሁኑ ወቅት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየካቲት ወር 2018 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፤ ኮሚሽኑ የተጣለበትን ታሪካዊ ኃላፊነት በብቃትና በጥራት እንዲወጣ ለማስቻል የሥራ ዘመኑ እስከ ጥቅምት 2019 ዓ.ም እንዲራዘም ተደርጓ።
ይህ የጊዜ ማራዘሚያ ኮሚሽኑ የቀሩትን የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎች በዝርዝር እንዲያጠናቅቅና በመላ ሀገሪቱ የተሰበሰቡ ግብዓቶችን በጥልቀት እንዲተነትን ምቹ ዕድል የሚፈጥር ነው። ከዚህ ጎን ለጎን፣ ኮሚሽኑ የምክክር ሂደቱን የሚያቀላጥፉ አወያዮችን የመምረጥና የማሰልጠን ሥራውን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑ፤ የሂደቱን ተአማኒነት፣ ገለልተኝነትና አካታችነት ይበልጥ የሚያጠናክር ተግባር ነው።
የካናዳ ፈር-ቀዳጅ ተሞክሮ፡ በጥናት ላይ የተመሠረተ ምክክር
በታላቅ የለውጥ ጉዞ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከካናዳ የረጅም ዘመን የምክክር ተሞክሮ የምትቀስመው ትምህርት እጅግ የጎላ ነው። ካናዳ ብዝኃነቷን የጥንካሬዋ መሠረት ያደረገችው በተከታታይ እና በታቀዱ ሀገራዊ ምክክሮች አማካኝነት ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው እ.ኤ.አ. በ1963 የተቋቋመው የባለ ሁለት ቋንቋ እና ባለ ሁለት ባሕል ንጉሣዊ ኮሚሽን ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በወቅቱ በሀገሪቱ ላይ ተጋርጦ የነበረውን የመበታተን አደጋ ለመቀልበስ የተጠቀመበት ቀዳሚ ስልት በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረተ ፖሊሲን መከተል ነበር።
ይህ ኮሚሽን ለሰባት ዓመታት ያህል ባደረገው ጥልቅ ምርምር እና ሕዝባዊ ውይይት፣ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ካናዳውያን በኢኮኖሚ እና በፖለቲካው መስክ የነበረባቸውን መገለል ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። የምክክሩ ውጤትም እ.ኤ.አ. በ1969 የኦፊሴላዊ ቋንቋዎች አዋጅ እንዲወጣ በማድረግ፣ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ እኩል እውቅና እንዲያገኙና ዜጎች በመረጡት ቋንቋ የመንግሥት አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል። ይህ ተሞክሮ እንደሚያረጋግጠው፤ ዘላቂ ሀገራዊ መግባባት የሚገነባው ስሜታዊ የሆኑ ትርክቶችን በመረጃ፣ በሐቅ እና በምክንያታዊ ውይይት መተካት ሲቻል ነው።
የዜጎችን ድምፅ የማዳመጥ ጥበብ፦ የስፓይሰር ኮሚሽን ትምህርት
ካናዳ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለገጠማት የሕገ-መንግሥት ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የተጠቀመችበት የዜጎች የምክክር መድረክ (Spicer Commission) ለኢትዮጵያ ሌላው ትልቅ ትምህርት ነው። ይህ መድረክ ከተለምዷዊ የፖለቲካ ልሂቃን ድርድር ወጥቶ፣ የውይይቱን ማዕከል በቀጥታ ወደ ዜጎች ያወረደ ነበር።
ኮሚሽኑ ቴክኖሎጂን በመጠቀም 75 ሺህ በላይ የዜጎችን ጥሪዎች ያስተናገደበት ነፃ የስልክ መስመር እና በመላ ሀገራችን የተካሄዱ የቡድን ውይይቶች ከ400 ሺህ በላይ ጎልማሶችን ማሳተፍ ችለዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ዜጎች በፖለቲከኞች ላይ የነበራቸውን ጥልቅ ቅሬታና ጥርጣሬ በግልጽ እንዲተነፍሱ መደረጉ፣ የምክክር ሂደቱ መተማመንን የመገንባት ታላቅ አቅም እንዳለው በተግባር አሳይቷል። ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት የልሂቃንን ድርድር ብቻ ሳይሆን፣ በየደረጃው ያለውን ማኅበረሰብ ድምፅ ለማዳመጥ የምታደርገው ጥረት፤ የካናዳን ዜጋ-ተኮር የምክክር ስልት አርአያ ያደረገ እንዲሆን ይጠበቃል።
የታሪክ ጠባሳዎችን ማከም፦ የእውነትና እርቅ ኮሚሽን ፋይዳ
ሌላውና እጅግ ወሳኙ የካናዳ ተሞክሮ፣ የታሪክ ቁስሎችን ከመፈወስ ጋር የተያያዘው የእውነትና እርቅ ኮሚሽን (TRC) ነው። ይህ ኮሚሽን ከሀገሬው ተወላጆች ጋር የነበረውን ዘመናትን የተሻገረ በደል ለመፍታት ለስድስት ዓመታት ባደረገው ጉዞ፣ ከ6 ሺህ 500 በላይ ሰለባዎችን በግንባር ቀደምነት አድምጧል። ኮሚሽኑ ያቀረባቸው 94 የተግባር ጥሪዎች (Calls to Action) ዛሬም ድረስ ካናዳን የማስተካከልና የማከም ሂደት ውስጥ እንደ መመሪያ እያገለገሉ ይገኛሉ።
የዚህ ኮሚሽን ስኬት ሚስጥር፤ የተፈጸመውን በደል “ባሕላዊ የዘር ማጥፋት” (Cultural Genocide) ብሎ በሐቅ እውቅና መስጠቱና መፍትሔዎቹን ወደ ሕግና ተቋማዊ አሠራር መቀየሩ ነው። ኢትዮጵያም በምክክር ሂደቷ የታሪክ ቁስሎችን ለማከም የምታደርገው ጥረት፣ እንደ ካናዳ ሁሉ ግልጽነትን፣ እውነተኛ ሐቅን ማውጣትንና ለተበዳዮች ተገቢውን እውቅና መስጠትን መሠረት ሊያደርግ ይገባል።
ኢትዮጵያ ከካናዳ የምትቀስማቸው ዋና ዋና የምክክር ስልቶች
ከካናዳ የምክክር ሞዴል የምንቀስመው ትልቁ ትምህርት፤ ምክክር ማለት በሁሉም ጉዳዮች ላይ መቶ በመቶ ስምምነት መፍጠር ማለት አለመሆኑን ነው። ይልቁንም ምክክር ልዩነቶችን ይዞ በሰላማዊ መንገድ አብሮ ለመኖር የሚያስችል “የተጋጨ መግባባት” (Conflictual Consensus) ላይ መድረስ መሆኑን ነው። ካናዳ በኩቤክ የመገንጠል ፍላጎት እና በቀሪው የሀገሪቱ ክፍል መካከል የፈጠረችው ስምምነት የዚህ ስልት ቀዳሚ ማሳያ ነው።
ሀገሪቱ ልዩነቶቿ በሕግ፣ በምክክር እና በተቋማዊ አሠራር እንዲፈቱ በማድረግ ሀገራዊ አንድነቷን ማጽናት ችላለች። ይህ ተሞክሮ ኢትዮጵያ እየተከተለችው ካለው የፌዴራሊዝም ሞዴል አንጻር ለማንነት ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ትልቅ ፋይዳ ያለው አቀራረብ ነው። በተጨማሪም የፖለቲካ ተዋናዮች ከመጠላለፍ ይልቅ በሐሳብ ብልጫ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
የጋራ ስምምነትን የመገንባት ተስፋ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱን ከሀገር ውስጥ እስከ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ ድረስ በስፋት በማከናወን፣ ወደ መጨረሻው የምክክር ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ምንም እንኳን በጸጥታ ሁኔታዎች እና ተግዳሮቶች ቢኖሩም፤ ኮሚሽኑ ሁሉንም ድምጾች የማካተት ቁርጠኝነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል። በተለይም በአካል ተገኝተው አጀንዳ መስጠት ላልቻሉ ዜጎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ አመቺ ሁኔታዎች መፈጠራቸው የሂደቱን አካታችነት ያረጋግጣል።
የካናዳ ተሞክሮ እንደሚያስተምረን፤ ሀገራዊ እርቅ በትዕግሥት፣ በሐቅ እና በዜጎች ንቁ ተሳትፎ የሚገነባ የረጅም ጊዜ ጉዞ ነው። ኢትዮጵያም ይህንን የሰለጠነ የምክክር መንገድ በመከተል፣ ልዩነቶቿን የጥንካሬዋ መሠረት የምታደርግበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ እንደምትከፍት ጽኑ እምነት አለ።
በለሚ ታደሰ