በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የሕግ የበላይነት የሰላም ዋስትና፣ የፍትሕ መረጋገጥ ደግሞ የዜጎች የኅሊና ዕረፍት አና የልማት መሠረት ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የተያያዘችው የ"መደመር" የለውጥ ጉዞ፣ በዋናነት ይህንኑ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ እና ፍትሕን ለሁሉም ተደራሽ የማድረግ ታላቅ ተልዕኮን አንግቦ የተነሣ ነው።
ይህ ጉዞ ከፖለቲካዊ ፍላጎት ባለፈ፣ ተጨባጭ ተቋማዊ ለውጦች እና በሕዝብ ሕይወት ላይ የታዩ ስኬቶች የተመዘገቡበት የታሪክ ምዕራፍ ሆኗል።
የፍትሕ እኩልነት - ከመርሕ ወደ ተግባራዊ ተጠያቂነት
ለረጅም ዘመናት የሕግ የበላይነት በንድፈ-ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሲጠቀስ ቆይቷል። በተግባር ግን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ባለሀብቶች ከሕግ በላይ የሚሆኑበት፣ ሕግ ደካማዎች ላይ ብቻ የምትሠራበት አዝማሚያ ጎልቶ ይታይ ነበር።
መንግሥት ይህንን ተቋማዊ ስብራት በመሻገር “ፍትሕ ለሁሉም፣ ተጠያቂነት በሁሉም ላይ” የሚለውን መርሕ የፖለቲካዊ እሳቤው ማዕከል አድርጎታል። ዛሬ ላይ ማንኛውም ዜጋ፣ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ጀምሮ እስከ ታችኛው ማኅበረሰብ ድረስ በሕግ ፊት እኩል የሚታይበት እና ለፈጸመው ጥፋት መልስ የሚሰጥበት ሥርዓት በተግባር እየታየ ይገኛል።
ይህ ተጠያቂነት በተለይም የሀገርን የኢኮኖሚ አቅም በሚያደቅቁ የሙስና ወንጀሎች ዙሪያ በግልጽ ታይቷል። በፌዴራል ደረጃ ብቻ ከ400 በላይ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ በሙስና የተሳተፉ ግለሰቦች ላይ ክስ መመሥረቱ፣ መንግሥት ለፍትሕ እና ለንጽህና ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ይህ እርምጃ “ከሕግ በላይ ማንም የለም” የሚለውን መልዕክት በተግባር ያስመሰከረ እና በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን (Social Contract) የገነባ ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።
ተቋማዊ ነፃነት እና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች
የፍትሕ ሥርዓቱን ከፖለቲካዊ ተጽዕኖ እና ከገዥው አካል ቀጥተኛ ጣልቃ-ገብነት ነፃ ማድረግ የለውጡ ዋነኛ ምሰሶ ነው። ባለፉት ዓመታት የዳኝነት እና የፍትሕ አካላት በገለልተኝነት እና በነጻነት እንዲሠሩ የሚያስችል ምቹ መደላድል ተፈጥሯል።
በሕግ ማሻሻያ ረገድም ኢትዮጵያ ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ ያስቆጠሩ እና ከዘመኑ ጋር የማይራመዱ የንግድ እና የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕጎችን በማሻሻል አዲስ ታሪክ ጽፋለች።
እነዚህ ሕጎች መሻሻላቸው ለሀገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት እና ለውጭ ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠራቸውም በላይ፣ ዜጎች ዘመኑን የዋጀ የሕግ ጥበቃ እንዲያገኙ ያደርጋል።
በተጨማሪም የግልግል ዳኝነት እና የዕርቅ አሠራር ሥርዓት ዐዋጅ መውጣቱ፣ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ብቻ ተቀፍድደው እንዳይቀሩ እና በአማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች (ADR) ፈጣን መፍትሔ እንዲያገኙ ትልቅ በር ከፍቷል።
የሪፎርሙ ተጨባጭ ውጤቶች በዜጎች ሕይወት
የሪፎርም ሥራዎቹ በዜጎች ሕይወትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያመጡት ውጤት ተጨባጭ ነው። በዚህም በሙስና እና በኢኮኖሚ ወንጀል ተመዝብሮ የነበረ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሕዝብ እና የሀገር ንብረት ተመላሽ ሆኖ ለልማት እንዲውል ተደርጓል። በአማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች መጠናከር እና በፍትሕ አካላት የአቅም ግንባታ ምክንያት፣ ጉዳዮች በፍርድ ቤት የሚቆዩበት ጊዜ አሽቆልቁሏል።
ይህም ዜጎች ለዓመታት በፍርድ ቤት ደጅ በሚያደርጉት መመላለስ የሚባክን ጉልበታቸውን እና ገንዘባቸውን እንዲቆጥቡ ረድቷል። በተጨማሪም ተቋማዊ የቁጥጥር ሚዛን ሥርዓት በመጠናከሩ፣ በሕግ አስፈጻሚዎች የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች በአስተዳደራዊ እና በሕግ እርምጃ እንዲታረሙ መደረጉ ሌላው የለውጡ ስኬት ነው።
የወደፊቱ ራዕይ - ዲጂታላይዜሽን እና ተደራሽነት
ኢትዮጵያ አሁን ላይ የፍትሕ ሥርዓቷን ወደ ዲጂታል እና የላቀ የተደራሽነት ምዕራፍ ለማሸጋገር እየሠራች ትገኛለች። “የፍትሕ መሶብ” በተባለው የዲጂታላይዜሽን ፕሮጀክት አማካኝነት አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ ለማድረግ ታቅዷል። የኤሌክትሮኒክስ የክስ መዝገብ፣ የበይነ-መረብ ቀጠሮ እና የቨርችዋል ዳኝነት ሲስፋፉ፣ ፍትሕ በቦታ እና በጊዜ ሳይገደብ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል።
የሰው ኃይል ብቃትን ለማሳደግም የዳኞች ነጻነት እና ተጠያቂነትን የሚያመጣጥን ሥርዓት በመዘርጋት፣ በሥነ-ምግባር የታነጹ ባለሙያዎችን የማሰማራት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
ከዚህም ባለፈ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶች ተቋማዊ ሆነው እንዲጎለብቱ በማድረግ፣ ቀላል እና ወጪ ቆጣቢ ፍትሕን ለማስፈን የሚደረገው ጥረት የሀገርን ማንነት ከዘመናዊነት ጋር የሚያስተሳስር ድልድይ ነው።
በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የፍትሕ ሥርዓት ለውጥ፣ የሀገር ደኅንነት ስጋት የሆኑትን ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የሽብር ተግባር እና የሳይበር ወንጀሎችን በልዩ ስትራቴጂ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑ ይገለጻል። ለዘላቂ ሰላም ውይይት እና ይቅርታ አስፈላጊ ቢሆኑም ተጠያቂነት የሌለበት ይቅርታ ግን ለኢ-ፍትሐዊነት መንገድ ይከፍታል።
ስለሆነም፣ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት የመጠበቅ እና የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ የሚፈልጉ ኃይሎችን የመግታት ቀዳሚ ግዴታውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
የሕዝብን አመኔታ ያተረፈ፣ ገለልተኛ እና ብቁ የፍትሕ ሥርዓት በመገንባት ኢትዮጵያን ለዜጎቿ የፍትሕ መከታ፣ ለኢንቨስትመንት ደግሞ አስተማማኝ የሕግ ከባቢ ያላት ሀገር የማድረግ ግብን ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካል የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል።
በበረከት ሽመልስ