Search

"የእናቶች ጫና እንዲቀንስ፣ ውሳኔ ሰጪነታቸው እንዲረጋገጥ ሰርተናል፤ ተሳክቶልናል"፦ ከንቲባ አዳነች አቤቤ

እሑድ ግንቦት 02, 2018 51

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓለም አቀፍ የእናቶች ቀን ሴቶች የተሳተፉበት በ7ኛው ሀገራዊና ከተማ አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲን ዓላማና ግብ የሚደግፍ፣ ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
ከንቲባዋ በማለዳው በነበረው መርሃ ግብር ላይ ለተገኙት በርካታ ሴቶች ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ዕለቱ ሴቶች በ7ኛው ሀገራዊና ከተማ አቀፍ ምርጫ የብልፅግና ፓርቲን ዓላማና ግብ ለመደገፍ በደማቅ ሁኔታ የተሰባሰቡበት መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የሴቶችን ተጠቃሚነትና ቁልፍ ውሳኔ ሰጪነት ለማረጋገጥ በተገባው ቃል መሠረት ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ከንቲባዋ አስረድተዋል።
በተለይም የእናቶችን ጫና ለመቀነስ ልጆች ሁሉም ነገር ተሟልቶላቸው እንዲማሩ የተደረገው ጥረት፣ በአበበች ጎበና ስም የተሰየመ የእናቶችና የሕፃናት ሆስፒታል መገንባት እንዲሁም የ"ነገዋ" የሴቶች ተሃድሶና ልህቀት ማዕከል መቋቋም ዋና ዋናዎቹ ስኬቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የእንጀራ ፋብሪካዎችን ለሴቶች በመገንባትና ባለፉት ዓመታት ከተፈጠሩ ሁለት ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች ውስጥ 51 በመቶው ለሴቶች እንዲሆኑ በማድረግ የሴቶችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ክብር ማረጋገጥ መቻሉን አብራርተዋል።
በፖለቲካው ዘርፍ ያለውን ተሳትፎ በተመለከተም በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በከተማዋ ከቀረቡት እጩዎች መካከል 54 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን ከንቲባዋ ይፋ አድርገዋል።
በከተማዋ ምክር ቤት ከ40 በመቶ በላይ ሴቶች እንዲወከሉ መደረጉ የሴቶች ሚና ለአጃቢነት ሳይሆን የውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን በማመን የተከናወነ ተግባር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
የምርጫ ምልክታቸው የሆነውን የሥንዴ ነዶ በመጥቀስም፣ ልክ እንደ ነዶው ተደምሮ ማንንም ያልዘነጋ አካታች ልማትን ለማረጋገጥና የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማስቀጠል ፓርቲያቸው ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የከተማዋን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ አብረው ለቆሙት ሴቶች ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ጉዞአቸው በመደመር መንፈስ ወደ ብልፅግና እንደሚቀጥልና ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገርነት ለማሸጋገር በትጋት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።