የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገታቸውን ለማፋጠንና የዜጎቻቸውን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የኃይል አቅርቦታቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በተለይም አህጉሪቱ በታዳሽ ኃይል ልማት ረገድ ያላት ሰፊ እምቅ ሀብት ለበርካታ ሀገራት አዲስ ተስፋን የሰጠ ሲሆን፣ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ለሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን በጊጋዋት ሰዓት (GWh) ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 የአፍሪካ ሀገራት በዘርፉ ያላቸው ከፍተኛ ተሳትፎ ተጠቅሷል፡፡
ዓለም አቀፉ የሃይል ተቋም መረጃ እንደሚያመልክተው ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ስትጠቀስ፣ ኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ዓመታት የኃይል ማመንጨት አቅሟን ከእጥፍ በላይ በማሳደግ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ በማስገባት ከአህጉሪቱ ግንባር ቀደም የኃይል አምራቾች ተርታ ተሰልፋለች፡፡
አንድ ጊጋዋት ሰዓት (1 GWh) ኃይል ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ለሚገኙ ወደ 360 ለሚጠጉ መካከለኛ አባወራዎች ለአንድ ዓመት የሚበቃ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መስጠት የሚችል ነው።
በመሆኑ ይህ የምርት መጠን እድገት ሀገራቱ የውስጥ ፍጆታቸውን ከማሟላት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ መንገድ እየከፈተላቸው ይገኛል፡፡
የአፍሪካ የኃይል ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ አለመሆናቸው ይታወቃል፡፡
በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ግብፅ ያሉ ሀገራት የጀመሩት የኃይል ልማት ተጠናክሮ መቀጠል ለአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ከፍተኛ ኤሌክትሪክ አምራችነት ስማቸው በጉልህ የተጻፉ ሀገራት ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ሊቢያ፣ ጋና፣ ቱኒዚያ እና ሞዛምቢክ መሆናቸው ተጠቅሷል።
በሃይማኖት ከበደ