ታሪክ እንደሚያስተምረን ታላላቅ ሀገራት የተገነቡት በተመቻቸ ጎዳና ተረማምደው ሳይሆን፣ በከባድ ፈተናዎች እና በነደደ ብሔራዊ ቁጭት ውስጥ አልፈው ነው። የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ፣ ዛሬ ላይ ከቀላል የታሪክ ናፍቆት እና ከትዝታ ማዕቀፍ ወጥቶ፤ ወደ ጥልቅ ሀገራዊ ቁጭት፣ የህልውና ትግል እና የተግባራዊ ትውልድ ንቅናቄነት ተሸጋግሯል። አባቶቻችን በደም በተጠመቀ መስዋዕትነት አልፈው፣ ይህችን ድንቅ ምድር ሲዋጁን የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ በሳይንስ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በስትራቴጂካዊ ብልሃት ታጥቆ ሀገሪቱን ከገባችበት የ"የየብስ እስረኝነት" (Geographic Prison) ሰብሮ የማውጣት ታሪካዊ የትውልድ ኃላፊነት በትከሻው ወድቆበታል። ይህን ኃላፊነት በግብታዊ ስሜት ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችን በቀመረ እና መረጃን መሠረት ባደረገ አካሄድ መምራትን የግድ ይላል።
ዓለም አቀፉን ተሞክሮ ስንቃኝ፣ የባህር በር እና የውሃ ላይ ኃያልነት የአንድን ሀገር የኢኮኖሚ አቅጣጫ እንዴት እንደሚቀይረው በግልጽ እንረዳለን። ታላላቅ ለውጦች የመጡት በመከራ ውስጥ በተፈጠረ ጠንካራ ብሔራዊ መንፈስ ነው። ቻይናውያን በ19ኛው ክፍለ ዘመን በባህር በኩል የመጡባቸው ወራሪዎች ያደረሱባቸውን "የውርደት ዘመን" (ከ1839 እስከ 1949) እንደ ከባድ የውድቀት ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ታላቅ ብሔራዊ የትግል ስንቅ ተጠቅመውበታል። "በባህር ደካማ በመሆናችን ተደፈርን" የሚለው መራራ እውነት እና ቁጭት፣ ዛሬ ላይ ቻይናን የዓለም የንግድ እና የባህር ኃይል ቁንጮ እንድትሆን አድርጓታል። "ባህርን የተቆጣጠረ ዓለምን ይቆጣጠራል" የሚለውን የጂኦ-ፖለቲካዊ ሀቅ በተግባር አሳይተዋል።
በሌላ በኩል፣ ደቡብ ኮሪያ በ1953 የኮሪያ ጦርነት ማብቂያ ላይ ምንም ዓይነት የተፈጥሮ ሀብት ያልነበራት፣ በጦርነት የደቀቀችና ድሃ ሀገር ነበረች። ነገር ግን "የሃን ወንዝ ተአምር" በሚል በተሰየመው የአንድ ትውልድ ቆራጥ የለውጥ ጉዞ፣ ከድህነት አረንቋ ለመውጣት ባደረጉት የጋራ ቁጭት እና በትምህርት ላይ ባፈሰሱት መዋዕለ ንዋይ፣ ዛሬ ላይ በዓለም አንደኛዋ ግዙፍ መርከብ አምራች እና የዘመናዊ ወደብ መሪ ለመሆን በቅተዋል። ይህ የትውልድ ቆራጥነት በሲንጋፖርም ደግሞ በጉልህ ታይቷል። በ1965 ተስፋ ያልነበራትና በረግረግ የተከበበች ደሴት የነበረችው ሲንጋፖር፣ "የማይቻል ነገር የለም" በሚል የፅናት መርህ የወደብ ግንባታ ላይ በማተኮሯ፣ ዛሬ በዓመት 41 ሚሊዮን ኮንቴይነሮችን የምታስተናግድ የዓለም ቀዳሚ የባህር ትራንዚት ማዕከል ሆናለች። ቬትናምም በተመሳሳይ በ1980ዎቹ በጦርነት የዛለ ኢኮኖሚዋን በ"ዶይ ሞይ" (Doi Moi) የለውጥ ንቅናቄ በማነቃቃት፣ በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ የወደብ አቅሟን በ25 በመቶ በማሳደግ የዓለም አቀፍ ንግድ ተዋናይ ሆናለች።
ይህ የመለወጥ ፍላጎት በጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸው ፈተና ውስጥ ለነበሩ ሀገራትም ቢሆን አይቀሬ ነበር። በበረሃ አሸዋ የተከበበችው ዱባይ (የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ)፣ ወደብ አልባ የመሰለ መልክዓ-ምድራዊ ገጽታዋን ወደ በረከት ለመቀየር ባላት ራዕይ የ"ጅበል አሊ"ን (Jebel Ali) ግዙፍ ወደብ በመገንባት የዓለም ትልቁ ሰው ሰራሽ ወደብ ባለቤትና የንግድ ማዕከል ሆነች። እስራኤል በጠላት በተከበበችበትና የህልውና ስጋት በተደቀነባት ወቅት፣ ባህርን እንደ ብቸኛ የመፈናፈኛ እና የመኖር አማራጭ ወስዳ፣ የሃይፋ እና የአሽዶድ ዘመናዊ ወደቦችን ለስትራቴጂካዊ ጥበቃና ለኢኮኖሚ ዕድገት ተጠቅማባቸዋለች።
ባህር አልባ መሆንን (Landlockedness) በእልህ እና በብልሃት ያሸነፉ ሀገራት ተሞክሮም ለኢትዮጵያ ሌላኛው ትልቅ ትምህርት ነው። ሩዋንዳ በዘር ማጥፋት የወደመች መሬት ዝግ ሀገር ብትሆንም፣ የጂኦግራፊያዊ መነጠልን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በፈጣን አገልግሎት አሰጣጥ በማሸነፍ በአፍሪካ ቀዳሚ የንግድ ምቹነት ደረጃን ይዛለች። ስዊዘርላንድና ሉክሰምበርግ የተራራማነትና የጥበት ተግዳሮቶቻቸውን ቀጣናዊ ውህደትን በመፍጠር፣ ከፍተኛ እሴት ያላቸውን ምርቶች በማልማት እና የአገልግሎትና የፋይናንስ ማዕከል በመሆን አልፈውታል፤ ዛሬ የዓለም እጅግ የበለጸጉ ሀገራት ተርታ ይሰለፋሉ።
ኦስትሪያም ዘመናዊ መሠረተ ልማት በመዘርጋት ምርቷን በ9 ቀናት ውስጥ ወደ ውጭ መላክ ስትችል፣ ቦሊቪያ ደግሞ ባህር በማጣቷ የደረሰባትን የኢኮኖሚ ኪሳራ ለማካካስ ከሀገር ውስጥ ምርቷ (GDP) ከ5.4 በመቶ በላይ ለትራንስፖርት መሠረተ ልማት በመመደብ በፍጥነት እያደገች ትገኛለች። ካዛክስታን ከዓለም የባህር ጠረፍ 3,750 ኪሎ ሜትር ብትርቅም (ምርቷን ለመላክ 81 ቀናት ቢፈጅባትም)፣ ግዙፍ የየብስ ትራንስፖርት መስመሮችን በመዘርጋት የዓለማችን ትልቋ መሬት ዝግ ሀገር ሆና የንግድ ተወዳዳሪ መሆን ችላለች። ሞንጎሊያ በበኩሏ በሁለት ግዙፍ ሀገራት መሃል ብትገኝም፣ በባህር ህግ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖን በመፍጠር እና በዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) የመሬት ዝግ ሀገራትን መብት በማስከበር ዲፕሎማሲያዊ ድል ተቀዳጅታለች። ኡጋንዳ በአዋዛ የልማት ፕሮግራም የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን በማፋጠን እንዲሁም ቡሩንዲ የወደብ ወጪዋ ከዴንማርክ በ4 እጥፍ ቢበልጥም የድንበር ቢሮክራሲን ለመቀነስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (UN) ድጋፍ በቁጭት እየሰሩ ይገኛሉ።
እነዚህን ሁሉ ተሞክሮዎች እና የተረጋገጡ መረጃዎች ስንመዝን፣ አሁን ላይ ከ132 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት የኢትዮጵያ ጂኦግራፊያዊ እጣ ፈንታ ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ በጉልህ እንረዳለን። ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት በዓለም ላይ ትልቋ በመሬት የተዘጋች ሀገር ናት። ይህ መልክዓ-ምድራዊ እስር በሀገሪቱ ላይ እጅግ ከባድ የሆኑ ሁለንተናዊ ጫናዎችን እያሳደረ ይገኛል። የኢኮኖሚ ቀረጡን ብቻ ብንመለከት፣ ሀገሪቱ በየዓመቱ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የወደብ ኪራይ ክፍያ ትፈጽማለች። ይህ አስደንጋጭ አሃዝ ማለት፣ ኢትዮጵያ በየሦስት ዓመቱ አንድ የሕዳሴ ግድብ የሚያስገነባ ግዙፍ ኃብት ለሌላ ሀገር በኪራይ መልክ ትገብራለች ማለት ነው። በመሬት ዝግነት እና ተያያዥ የሎጂስቲክስ ማነቆዎች ምክንያት ብቻ፣ በየዓመቱ ከ13 በመቶ እስከ 23 በመቶ የሚሆን የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ዕድገት እናጣለን። የሎጂስቲክስ ወጪያችን ከጎረቤት ሀገራት በ60 በመቶ ከፍ ያለ በመሆኑ የተነሳ፣ ተራው ዜጋ ለዕለታዊ ሸቀጦች እና መሰረታዊ ፍላጎቶች ከ25 እስከ 30 በመቶ ተጨማሪ የኑሮ ውድነት ዋጋ እንዲከፍል ተገዷል። ይህ በየትኛውም መመዘኛ ሊቀጥል የማይችል ከባድ የኢኮኖሚ ደም መፍሰስ ነው።
ስለሆነም፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተራ የፖሊሲ ፍላጎት ወይም የፖለቲካ ቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን፣ ፍጹም የህልውና፣ የብሔራዊ ደህንነት እና የትውልድ ህይወት ጥያቄ ነው። የሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ እና መሰል ጥረቶች፣ ይህቺን ታላቅ ሀገር ከታሰረችበት የ"ጂኦግራፊ እስር ቤት" በሰላማዊ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለማውጣት የተጀመሩ የዘመኑ ታላላቅ ስራዎች ማሳያ ናቸው። ትውልዱ ይህንን ወርቃማ የታሪክ አጋጣሚ ሊያመልጠው አይገባም። አባቶቻችን የሀገርን ዳር ድንበር አስከብረው እንደቆዩልን ሁሉ፣ ይህኛው ትውልድ ደግሞ በዓለም አቀፍ ሴራና በአካባቢያዊ አሻጥር ያጣነውን የባህር በር የመመለስ እና ኢትዮጵያን የንግድ፣ የሎጂስቲክስ እና የባህር ኃይል ማዕከል የማድረግ የ"ዘመኑ አርበኝነት" ግዴታ አለበት። ወደ ባህር ሰብሮ መውጣት ምርጫ ሳይሆን፣ ይህች ሀገር የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት እና ለቀጣዩ ትውልድ ነጻ፣ የበለጸገችና በራሷ የምትቆም ጠንካራ ሀገር ለማስረከብ የሚያስችል ብቸኛና ታላቅ የድል አሻራ ነው። ትውልዱ በሳይንስ፣ በዘመናዊ ዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ግንባታ ቆርጦ በመነሳት ታሪካዊ አጋጣሚውን በእጁ ሊያስገባ ይገባዋል! ታሪክ የሚሰራው በቁጭት ነው፤ ያ ቁጭት ደግሞ የዚህ ትውልድ የልብ ትርታና የተግባር መገለጫ ሊሆን ይገባል!
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ