በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተሰባሰቡ የይዘት ፈጣሪዎች፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካውያን ሁሉ የጋራ ቤት መሆኗን በታላቅ አድናቆት ገልጸዋል።
ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው የታዘቧትን አዲስ አበባ "ውብ፣ ንፁህ እና ሳቢ" ሲሉ ነው የገለጿት።
ዩጋንዳዊው የይዘት ፈጣሪ ሳዲ ሶዚ በከተማዋ ውበት መማረኩን ሲገልጽ፤ "አዲስ አበባ እጅግ ቆንጆ፣ ንፁህ እና ማራኪ ናት፤ ማንኛውም ሰው ሊጎበኛት ይገባል ብዬ አምናለሁ" ብሏል።
ከደቡብ ሱዳን የመጣችው ራያ ራያ በበኩሏ በኢትዮጵያውያን መስተንግዶ መደሰቷን ገልጻ፤ "እዚህ ያለው መስተንግዶ በእውነት ድንቅ ነው፤ የተቀበሉን በታላቅ ፍቅር ነው" ስትል ምስክርነቷን ሰጥታለች። አክላም ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ቤቷ እንደምትቆጥራትና ወደፊትም ተመልሳ እንደምትመጣ ገልጻለች።
ኬንያዊው ኤልቪስ ሙሽላ በበኩሉ "ከተማዋ እጅግ ማራኪ እና የተደራጀች ናት" ካለ በኋላ፤ እኛ አፍሪካውያን ይበልጥ በመጠናከር አፍሪካ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን ለዓለም የምናሳይበት የጋራ ዘመቻ ሊኖረን ይገባል ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ከቡርኪና ፋሶ የመጣው ጃጓርም በኢትዮጵያ ባየው ዕድገትና በሕዝቡ የሥራ ተነሳሽነት መደሰቱን ጠቁሞ፣ ጉብኝቱ ለሥራው አዳዲስ ዕድሎችን እንደፈጠረለት ገልጿል።
ናይጄሪያዊው አዲናካ በበኩሉ፤ ማኅበራዊ ሚዲያ ራሳችንን ለዓለም የምናስተዋውቅበት ሰፊ መድረክ ፈጥሯል ሲል ገልጾ፤ "ስለ ባህላችን እና እሴቶቻችን ግንዛቤ በመፍጠር የአህጉራችንን ገጽታ መገንባት አለብን" ብሏል።
ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ በቆይታቸው የታዘቧቸውን አዎንታዊ እሴቶች፣ ውብ የቱሪስት መስህቦች እና የሕዝቡን እንግዳ ተቀባይነት ለተከታዮቻቸው በማጋራት የኢትዮጵያን ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ቃል ገብተዋል።
በላሉ ኢታላ