Search

የባሕር በር ለኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ እስረኝነት ወደ ህልውና ነፃነት

እሑድ ግንቦት 02, 2018 120

የባሕር በር ማጣት የሀገርን ኢኮኖሚ በማሰር፣ የንግድ ትንፋሽን የሚቀማ የህልውና ማነቆ ነው። ሀገራችን 130 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪ ፍላጎቷን ለማርካት ከዓለም ጋር የምትገናኝበት ሰፊና አስተማማኝ በር ያስፈልጋታል።

በመሆኑም ዛሬ ላይ የባሕር በር ጥያቄ የድንበር ወይም የግዛት የማስፋፋት ፍላጎት ሳይሆን፣ የኢኮኖሚ እስረኝነትን ሰብሮ የመውጣትና የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የማቅናት ትግል ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህ ጉዳይ ለሀገራችን "ህልውና" ጉዳይ ተብሎ የሚጠራው በዘፈቀደ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና ካጋጠማት መልክዓ-ምድራዊ መታጠር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

ለዚህም እንደ ዋና ምክንያቶች የሚጠቀሱት የኢኮኖሚ ጥገኝነት፣ ብሔራዊ ደህንነት፣ ስትራቴጂካዊ ስጋቶች እና የታሪክ አውዶች ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከዓለም ጋር የምታደርገው የንግድ ልውውጥ 95 በመቶ ገደማ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆኑ፣ በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለወደብ ኪራይና ለተለያዩ ክፍያዎች እንድታወጣ ያስገድዳታል።

ይህ የወደብ አገልግሎት ክፍያ በጨመረ ቁጥር ደግሞ እንደ ነዳጅ፣ መድኃኒት እና ማዳበሪያ ባሉ መሠረታዊ ቁሶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማስከተል የሀገራችንን የእድገት ጉዞ በከፍተኛ ሁኔታ ይገታዋል።

ከኢኮኖሚው ባለፈ ሀገራዊ ደህንነትን በተመለከተ፣ የራስ የባሕር በር አለመኖር በሌሎች ሀገራት ፍላጎትና ፖለቲካዊ ውሳኔ ስር እንድትወድቅ ያደርጋታል።

በተለይም ቀይ ባሕር በአሁኑ ወቅት የዓለም ኃያላን መንግስታት ፉክክር የሚታይበት ቀጠና በመሆኑ፣ ሀገራችን ጥቅሟን ለማስከበር የባሕር ኃይል መገንባትና የራሷ የሆነ ማረፊያ ማግኘቷ ለሉዓላዊነቷ ወሳኝ ነው።

በዓለም ላይ የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት መካከል ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር ያላት ቀዳሚ ሀገር እንደመሆኗ፣ ይህን ሕዝብ የሚያስፈልገውን የኢንዱስትሪ ግብዓት ለማቅረብ አማራጭ እና ቀጥተኛ የባሕር መንገድ ማግኘት ለነገ የማይባል ተግባር ነው።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የረጅም ዘመን የታሪክ ባለቤት እንደነበረች የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት የመጠቀም መብትን የሚደግፉ ዓለም አቀፍ ሕጎችም አሉ

ስለሆነም የባሕር በር ለኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይሆን የኢኮኖሚ ነፃነትን ለማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ እና እንደ ትልቅ ሀገር በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው።

በሃይማኖት ከበደ