በመካከለኛው ምስራቅ ለወራት የዘለቀውን ውጥረት ለማርገብና ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም አሜሪካ ላቀረበችው የሰላም እቅድ ኢራን በፓኪስታን ሸምጋዮች በኩል ምላሿን መላኳ ተሰምቷል።
ቢቢሲን የኢራን መገናኛ ብዙሃን ን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ይህ በኢራን በኩል የተሰጠ ምላሽ ለሰላም የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አዲስ ምዕራፍ ላይ አድርሶታል።
ምንም እንኳን የሰላም ስምምነቱ ይዘት ይፋ ባይደረግም፣ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት የቀረበው የሰላም ጥሪ የኢራንን የኒውክሌር መርሃ-ግብር ወደ ድርድር ሊያመጣ የሚችል ባለ 14 ነጥብ የመግባቢያ ሰነድ ላይ ያተኮረ ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ፔዝሽኪያን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የውይይት ወይም የድርድር ንግግር ማለት ማፈግፈግ ሳይሆን ግቡ የኢራንን ሕዝብ መብትና ብሔራዊ ጥቅም በቆራጥነት ማስጠበቅ መሆኑን በመግለጽ ለሰላም ድርድሩ ያላቸውን ዝግጁነት አመልክተዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን ጦርነት በፍጥነት እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ግምት አብዛኛው የዓለም ማህበረሰብ የቴህራንን የኒውክሌር አላማ ማስቆም አስፈላጊ መሆኑን የተረዳበት ወቅት ላይ መደረሱ ለጦርነቱ መቋጫ ትልቅ ተስፋ ሆኗል።
ባለፉት ወራት በአሜሪካና በእስራኤል በኩል የተጀመሩ የተኩስ አቁም ስምምነቶች አልፎ አልፎ መጣስ ቢታይባቸውም፣ አሁን የተጀመረው የሰላም ምላሽ ግን ለዘላቂ መፍትሔ መንገድ የሚከፍት መሆኑ ታምኖበታል።
ምንም እንኳን የሆርሙዝ ባህር መዘጋትና በኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ ለዓለም የነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት ቢሆንም፣ አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል የተጀመረው የሃሳብ ልውውጥ ውጥረቱን አርግቦ ወደ ሰላማዊ ድርድር ለመግባት ትልቅ ተስፋን የፈነጠቀ ክስተት ሆኗል።
በልዩ እሸቱ