በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ እጅግ ውድ እና ክቡር የሆነው ስጦታ እናት ናት። እናትነት በደምና በአጥንት ተከፍሎ ሕይወትን ለሌላ ሕይወት የማስተላለፍ፣ በምድር ላይ የሚታይ እውነተኛ የፍቅር ተዓምር ነው።
ዛሬ ይህንን የማይተካ ስብዕና እና የትውልድ መሠረት የሆነችውን እናትን በልዩ ሁኔታ የምናወድስበት፣ የፍቅር ዕዳችንንም የምንከፍልበት ልዩ ቀን ነው።
በዓለም ዙሪያ የሚከበረው የእናቶች ቀን፣ ስለ እናትነት ታላቅነት የምናስብበት፣ በዝምታ የከፈለችውን መስዋዕትነት የምናመሰግንበት እና ጥልቅ ፍቅራችንን የምንገልጽበት ዕለት ነው።
እናት ለልጆቿ የምትሰጠው ፍቅር ቅድመ ሁኔታ የሌለው፣ ከአምላክ ፍቅር ቀጥሎ ንጹህ እና የማይለወጥ የሕይወት ስንቅ ነው።
እርሷ የቤተሰብ ምሰሶ ብቻ ሳትሆን፣ ነገን የምትቀርጽ ታላቅ መሐንዲስ ናት። በደስታችን ጊዜ ደስታን የምታጥፍ፣ በጭንቃታችን ጊዜ ደግሞ መፅናኛ የምትሆን የሕይወታችን ብርሃን ናት።
እናትነት ትዕግስትን እና የማይበገር ጥንካሬን ይጠይቃል። ልጆቿን ለማሳደግ የምታልፍባቸው የሕይወት ውጣ ውረዶች፣ የምትከፍላቸው የጤና፣ የጊዜ እና የጉልበት መስዋዕትነቶች ሁሉ ለልጆቿ ያላትን ጥልቅ ፍቅር ያሳያሉ።
እናት በቤት ውስጥ አስተማሪ፣ ነርስ፣ መካሪ እና ሁለንተናዊ ደጋፊ ናት። ይህ ቀን በስጦታ ወይም በምግብ ግብዣ ብቻ የሚታለፍ መሆን የለበትም።
ይልቁንም ስላደረገችልን ሁሉ "አመሰግናለሁ" በማለት ከልብ የመነጨ ዕውቅና የምንሰጥበት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ እናቶች የሚመኙትን የልጆቻቸውን ቅርበትና ትኩረት የምንቸርበት ሊሆን ይገባል።
እናትነትን በአንድ ቀን መታሰቢያ ብቻ መዘከር ክብሯን አይመጥነውም። እናት በየቀኑ ልትከበር፣ ልትታዘዝ እና ልትወደድ የሚገባት የሕይወታችን ድምቀት ናት።
እናት ማለት መላው ዓለም ሊተካ የማይችለው ትልቅ ሀብት ናት። ለሁሉም እናቶች፣ ለወደፊት እናቶች እና እናትነትን በልባቸው ለተሸከሙ ሁሉ መልካም የእናቶች ቀን ይሁንላችሁ።
በሃይማኖት ከበደ