Search

ከሳን ፍራንሲስኮ እስከ አዲስ አበባ፡ የኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታሪክና የሉዓላዊነት ትስስር

እሑድ ግንቦት 02, 2018 71

የኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ግንኙነት በዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት የሚቃኝ ብቻ ሳይሆን፣ በጽኑ የነፃነት ተጋድሎ እና በዓለም አቀፍ የሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ ጥልቅ ታሪካዊ መስተጋብር ነው።

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 1945 የድርጅቱ መሥራች አባል ስትሆን፣ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት እና የሉዓላዊነት ተምሳሌት በመሆን የሳን ፍራንሲስኮውን ቻርተር ከፈረሙ 51 አገራት መካከል አንዷ ነበረች።

ይህ ታሪካዊ መሠረት ዛሬ አዲስ አበባን የፓን አፍሪካኒዝም ማዕከል እና የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) መቀመጫ በማድረግ፣ አገራችን በአህጉራዊና በዓለም አቀፋዊ መድረክ ያላትን ተፈላጊነትና ተሰሚነት ከፍ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ እና የተመድ ግንኙነት ጥንካሬ የሚመነጨው ባለፈው ክፍለ ዘመን በሊግ ኦፍ ኔሽንስ መድረክ ከታየው መራራ ዲፕሎማሲያዊ ክህደት ነው። ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት የዓለም ማህበረሰብ ያሳየው ዳተኝነት ለድርጅቱ መፍረስና ለሁለተኛው ዓለም ጦርነት መባባስ ምክንያት መሆኑን የተረዳችው ኢትዮጵያ፣ አዲሱ ተመድ ጠንካራ የጋራ መከላከያ መርህና የአባል ሀገራትን ሉዓላዊነት የሚያከብር እንዲሆን በጽኑ ተሟግታለች።

ይህ ከታሪክ የተገኘ ትምህርት ኢትዮጵያ ዛሬም ለባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያላትን ታማኝነት በተግባር እንድታረጋግጥ አስችሏታል። በቅርቡም 171 ድምፅ ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧ፣ በዓለም አቀፍ ፖሊሲዎች ዙሪያ በተለይም የታዳጊ አገራትን የልማት መብት ለማስከበር ያላትን ተቀባይነት ዳግም አድሶታል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም ያላት ጽኑ አቋም በተግባር የተፈተነና የተመሰከረለት ነው። ከኮሪያ ጦርነት የቃኘው ሻለቃ ጀግንነት ጀምሮ በኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያና ዳርፉር የሰላም አምባሳደርነቷን አስመስክራለች።

በአሁኑ ወቅት በአብዬ (UNISFA) እና በደቡብ ሱዳን (UNMISS) የምትጫወተው ሚና በቀጣናው ያላትን የጸጥታ ዋስትና አጉልቶታል።

በተለይም በአብዬ ተልዕኮ ውስጥ ያላት ብቸኛ ሰላም አስከባሪነት ሚና በድርጅቱ ታሪክ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ሲሆን፣ ይህም ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ደኅንነት የምትከፍለውን መስዋዕትነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

በልማትና በኢኮኖሚው ዘርፍም የኢትዮጵያና የተመድ አጋርነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ኢትዮጵያ የምታካሂደው ሁሉን አቀፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተመድ ዘንድ እውቅናን አትርፏል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ንጹህና ተመጣጣኝ ኃይልን በማቅረብ (SDG 7) ረገድ ያለውን ሚና የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲገነዘብ የተደረገው ጥረትም የዲፕሎማሲው ስኬት አካል ነው።

በተጨማሪም 2030 በአፍሪካ 300 ሚሊዮን ዜጎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመውን "Mission 300" የተሰኘውን ዓለም አቀፍ ኢኒሼቲቭ መቀላቀሏ፣ ሀገራችን በታዳሽ ኃይል ያላትን እምቅ አቅም ለቀጣናዊ ብልጽግና ለማዋል ያላትን ዝግጁነት ያሳያል።

የኢትዮጵያ ተፈላጊነት ምስጢር በሀገር ውስጥ ከሚከናወኑ ዓለም አቀፍ ፋይዳ ካላቸው ሥራዎች ጋር የተቆራኘ ነው።

የተመድ ዋና ጸሐፊ "የአፍሪካ ተስፋ" ብለው የገለጹት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ፣ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የምትሰጠውን ተግባራዊ ምላሽ ለዓለም አርአያ አድርጎታል።

ከታሪካዊው መሥራችነት እስከ ዘመናዊው የሰላም ማስከበርና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ የኢትዮጵያና የተመድ ግንኙነት በጋራ ጥቅምና በዓለም አቀፍ ተዓማኒነት ላይ የተገነባ የዘመናት ድልድይ ሆኖ ቀጥሏል።

በመሀመድ ፊጣሞ