Search

ፈተናዎችን ያለፈው የሀላባ እግር ኳስ ለታሪክ ሰሪዎቹ የመሬትና የገንዘብ ሽልማት ተበረከተላቸው

እሑድ ግንቦት 02, 2018 51

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ክለቡን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ማሳደግ ለቻሉት የሀላባ ከተማ እግር ኳስ ቡድን አባላት፣ ዛሬ በሀላባ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በተገኙበት ደማቅ ሕዝባዊ አቀባበልና የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ተከናውኗል።
በ2018 የውድድር ዘመን የከፍተኛ ሊጉ አሸናፊ በመሆን ወደ 2019 የሲቢኢ (CBE) ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊነቱን ያረጋገጠው ክለቡ፣ በዛሬው ዕለት ከዞኑ አስተዳደር ለእያንዳንዱ የቡድኑ አባል የ120 ካሬ ሜትር የመሬት ስጦታና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶለታል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙህዲን ሁሴን፣ ይህ ወቅት የሀላባ ስፖርት ጮራው የፈነጠቀበት ወርቃማ ጊዜ መሆኑን ገልጸው፤ የዘመናችን ጀግንነት እንደ ሀላባ ከነማ በብዙ መሰናክሎች ውስጥ አልፎ ስኬት ማስመዝገብ መሆኑን አብራርተዋል።
በተያያዘም የሀላባ ከተማ ከንቲባና የክለቡ ፕሬዚዳንት አቶ ገመዳ መሐመድ የሀላባ እግር ኳስ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር የተከፈለበት ታሪካዊ ስፖርት መሆኑን አስታውሰዋል።
ለዚህም ማሳያ እንዲሆን፣ ከዚህ ቀደም ቡድኑን ለመደገፍ ወደ ድሬዳዋ ሲጓዙ በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችና አደጋ የደረሰባቸው ደጋፊዎች የዞኑ አስተዳደር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
ይህ በድል የታጀበው ታሪካዊ ጉዞ እግር ኳስ ወዳዱን የሀላባ ሕዝብ ከማስደሰት ባለፈ፣ ከተማዋን የዓለም አቀፍ ስታዲየም ባለቤት ለማድረግና በሀገሪቱ እግር ኳስ ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ቡድን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ መነቃቃት ፈጥሯል።
ሀላባ ከተማ ወደ ከፍተኛው የሊግ እርከን መመለሱ፣ በቀጣዩ ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ላይ አዲስና ብርቱ የፉክክር መንፈስ ይዞ እንደሚመጣ የስፖርት ቤተሰቡ በታላቅ ተስፋ እየጠበቀው ይገኛል።
 
በአብርሃም አድማሱ