Search

ስምንት አስርት ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ እና የተመድ የዲፕሎማሲ ጉዞ

እሑድ ግንቦት 02, 2018 70

ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መሥራች አባላት አንዷ በመሆን የጀመረችው የ80 ዓመታት ታሪካዊ አጋርነት፣ ሀገራችን በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ጽኑ አቋም የሚያሳይ ነው።
ይህ የቆየ ግንኙነት በተለይም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ያላትን ንቁ ተሳትፎ እና ቀጠናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት ዕውቅና የሚሰጥ ነው።
በተለይም በቅርቡ ኢትዮጵያ በብሪክስ (BRICS) አባልነት መመረጧ፣ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤትና በዓለም የምግብ ፕሮግራም ቦርድ ውስጥ ያላት ንቁ ተሳትፎ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እና ክብደት የበለጠ አጠናክሮታል። ይህ አጋርነት በልማት፣ በሰብዓዊ ድጋፍና በጋራ ደህንነት ላይ ያተኮረ ሆኖ ቀጥሏል።
ዛሬ ላይ አዲስ አበባ ከ137 በላይ የውጭ ሀገራት ኤምባሲዎችና የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆን፣ ከኒውዮርክ እና ጄኔቫ ቀጥላ የዓለም ዲፕሎማሲ ስበት ማዕከል ሆናለች።
የዓለም መሪዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ትኩረት ሀገራችን የምትከተለው ነፃ፣ ሚዛናዊና ገቢራዊ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውጤት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋ ፈጣን ለውጥ፣ አስደናቂው የኮሪደር ልማት፣ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ግንባታ እና ሌሎች ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች አዲስ አበባን ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ አድርጓታል።
በ2017 ዓ.ም. ብቻ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት ማስተናገድ መቻሏ የከተማዋን ዲፕሎማሲያዊ ብቃት የሚያረጋግጥ ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች ኩራትና የአፍሪካ ድምፅ ሆና መውጣቷ፣ አዲስ አበባም “የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ” ሆና መቀጠሏን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
በመሐመድ ፊጣሞ