Search

ከመገለል ወደ ማዕከልነት፦ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት

ሰኞ ግንቦት 03, 2018 195

በአፍሪካ ቀንድ ያለው ጂኦ-ፖለቲካዊ ገጽታ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ማዕከላዊነት ዳግም እያረጋገጠ ይገኛል።

ሀገራችን ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረችበት ዓለም አቀፋዊ ጫና ተላቅቃ፣ ዛሬ የቀጣናው የሰላም እና የፀጥታ ዋስትና ሆና ቀርባለች።

ይህ ስኬት በ"መደመር" ፍልስፍና የሚመራው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነት ያስጠበቀ አመርቂ ውጤት እያመጣ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።

ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ የዓለም ኃያላን ሀገራት ለኢትዮጵያ ያላቸው አመለካከት ተቀይሮ፣ ለቀጣናዊ መረጋጋት ያላትን የማይተካ ሚና በመረዳት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ለመፍጠር ዐይናቸውን አዲስ አበባ ላይ ጥለዋል።

መደመር እንደ ስትራቴጂያዊ መሪ እና የዲፕሎማሲው ስኬት

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እሳቤ የመደመር ፍልስፍና የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት በአዲስ መልክ የቃኘ ስትራቴጂያዊ ኮምፓስ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ይህ ፍልስፍና የቀጣናውን ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነትን በማስቀደም የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ከቀጣናዊ ብልጽግና ጋር የሚያስተሣሥር ነው።

በመደመር መንግሥት እሳቤ የተቀረጸው እና ፍሬያማ ለውጥ እያመጣ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ምሰሶዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎቿ ክብር ናቸው።

ወደ ውጭ ሲወጣ ደግሞ "ቅድሚያ ለጎረቤት" ብሎ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ከጥርጣሬ እና ከስጋት ወደ ትብብር እና የጋራ ልማት ቀይሮታል።

ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ እየሰፋ ሲሄድም ከየትኛውም ርዕዮተ ዓለም ወገን ሳይወግን ለኢትዮጵያ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ እንዲሁም ራስን ከማግለል ወጥቶ ተሳታፊ፣ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወጥቶ አጀንዳ አቀባይ የሆነ ነው።

ለዚህም ትልቁ ማሳያው ኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማትን እና የአየር ንብረት ለውጥን ጉዳይ ከራሷ ወደ አፍሪካ፣ ከዚያም አልፎ ወደ ዓለም አቀፍ ጠረጴዛ እያመጣች ያለችበት መንገድ በቂ ነው።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን ያለ ውጭ ጣልቃ ገብነት የመምራት አቅሟን በተግባር በማስመስከር የሉዓላዊነት ድል ተቀዳጅታለች።

አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ መሪዎች መገናኛ ማዕከል

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ተፈላጊነት መጨመሩን የሚመሰክረው ዋነኛው ማሳያ በርካታ የዓለም መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ጉብኝት ነው።

በቅርቡ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዮሐን ዋዴፑል፣ የሳዑዲ ዓረቢያው ልዑል ፈይሰል ቢን ፋርሃን፣ እና የአሜሪካው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው ወደ አዲስ አበባ ያደረጓቸው ጉብኝቶች የሀገራችንን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ያረጋገጡ ናቸው።

በተጨማሪም በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከኢትዮጵያ ልምድ እየወሰዱ ያሉት፣ ኢትዮጵያን ዛሬም እንደ ትናንቱ የነጻነት ጎዳና ለአፍሪካ ያላትን አርአያነት እጅግ እያጎላው የመጣ ነው።

በቅርብ ጊዜ ብቻ የቡሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሞዛምቢክ መሪዎች በተናጠል ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በአንድ ወቅት እንዳሉት ‘ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት’ መሆኗን እያረጋገጠ የመጣ ነው።

የስትራቴጂያዊ ወዳጅነት እና የኢኮኖሚ ትብብር መጎልበት

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት እያደገ መምጣቱ በተግባራዊ የኢኮኖሚ ትብብሮች እየታየ ይገኛል።

ሀገራችን በፈረንጆቹ 2024 የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር የምታደርገው ስኬታማ ግንኙነት በምሥራቅ እና በምዕራብ መካከል ያላትን ስትራቴጂያዊ ሚዛን ያሳያል።

አሜሪካ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቷ እና የአውሮፓ ኅብረት የ240 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ የልማት ፕሮግራም ይፋ ማድረጉ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያላትን አስፈላጊነት የሚያረጋግጡ ናቸው።

የባሕር በር ጥያቄ እና የዲፕሎማሲያዊ ድል ጉዞ

ለዘመናት የኢትዮጵያ የትውልድ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት በአሁኑ ወቅት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ትልቅ እመርታ እያስመዘገበ ይገኛል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያን ከባሕር መገለል እንደ "ጂኦግራፊያዊ እስር ቤት" በመመልከት ለሀገራችን የኢኮኖሚ ሕልውና ወሳኝ መሆኑን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስረዳት ረገድ ተሳክቶለታል።

ይህም በርካታ ሀገራት ኢትዮጵያ በሴራ ተገልላ ወደቆየችበት ቀይ ባሕር የመመለስ ሉዓላዊ መብት እንዳላት በመርሕ ደረጃ እንዲቀበሉ አድርጓቸዋል።

የቀጣናዊ ፀጥታ ዋስትና እና የኢትዮጵያ ሚና

ኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ላይ ያላት ጽኑ አቋም እና ለቀጣናዊ መረጋጋት የምታበረክተው አስተዋጽኦ ለዓለም ሰላም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ሀገራችን የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና ፀጥታ ምክር ቤት ሰብሳቢነትን በመረከብ በቀጣናዊ ግጭቶች አፈታት ላይ ያላትን ተፅዕኖ አሳድጋለች።

በሶማሊያ ያለውን ሽብርተኝነት ለመዋጋት እና የቀጣናውን ሰላም ለማስከበር የምታደርገው መሥዋዕትነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።

ኢትዮጵያ በብልሃት እና በመደመር እሳቤ የምትመራው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሀገራችንን በዓለም መድረክ ተፈላጊነቷ እንዲጨምር፣ ብሔራዊ ጥቅሟ እንዲከበር እና የዜጎቿ ክብር ከፍ እንዲል በማድረግ ረገድ ታላቅ ስኬት እያመጣ ይገኛል።

በለሚ ታደሰ