ቀዳማይ ልጅነት የሀገር መጻኢ ዕጣ ፈንታ የሚታነጽበት መሠረት ነው።
ይህ ምዕራፍ ከጽንሰት ጀምሮ እስከ ስምንት ዓመት ያለውን የሕፃናት ዕድሜ የሚሸፍን ሲሆን፣ የሰው ልጅ አእምሮ ከ90 በመቶ በላይ የሚገነባበትና ለቀሪው የሕይወት ዘመን የሚሆኑ መሠረታዊ ክህሎቶች የሚቀረጹበት ወሳኝ ወቅት ነው።
ሕፃናት በአካላዊ፣ በሥነ-አእምሮአዊ እና በማኅበራዊ ግንኙነት ረገድ ብቁ ሆነው እንዲያድጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግበትና ለትምህርት ዝግጁ የሚሆኑበት ጊዜ ተደርጎም ይወሰዳል።
የአንድ ሀገር የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕድገት መሠረቱ በእነዚህ ዓመታት በሚደረግ ኢንቨስትመንት ላይ የተመሰረተ ነው።
ለትውልድ እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያም ከድህነት ለመውጣትና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ቀዳማይ ልጅነትን እንደ ዋና ስትራቴጂ ወስዳ በልዩ ትኩረት እየሠራችበት ትገኛለች።
በቀዳማይ ልጅነት ወቅት ለሕፃናት የሚደረገው እንክብካቤ "ሁለንተናዊ የልጅነት እንክብካቤ" በሚባል ማዕቀፍ የሚመራ ነው።
ይህም የተሟላ ጤና፣ በቂ የተመጣጣኝ ምግብ አቅርቦት፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ አካባቢ፣ ለልጆች ጥያቄ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አስተዳደግ እና ቀድሞ የመማር ዕድሎችን ማግኘትን ያካትታል።
በዚህ ዕድሜ ውስጥ ለሕፃናት የሚሰጥ የፍቅርና የቅርብ ክትትል ለአእምሮ ዕድገታቸው እጅግ አስፈላጊ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ያለው ማኅበረሰባዊ ግንዛቤ አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
የሕፃናት መቀንጨርን ለመከላከል በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺህ ቀናት ውስጥ የሚደረግ የአመጋገብ ክትትልና የክትባት አገልግሎት ትልቅ ትኩረት የሚሻ የጥንቃቄ መስክ ነው።
ሕጻናት የተሟላ የጤናና የትምህርት አገልግሎት ካላገኙ ወደፊት የሚኖራቸው ምርታማነት 38 በመቶ ብቻ እንደሆነ የዓለም ባንክ መረጃ ያመላክታል።
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ በቀዳማይ ልጅነት ላይ የምታደርገው ኢንቨስትመንት ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ ትርጉም አለው የሚባለው።
በመጀመሪያዎቹ የልጅነት ዓመታት ላይ መሥራት የሀገርን የሰው ኃይል ምርታማነት ለመጨመር፣ የዜጎችን ገቢ ለማሳደግና ወደፊት ለማኅበራዊ ደኅንነት የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ በእጅጉ ይረዳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ተገንዝቦ በ2011 ዓ.ም እና በ2013 ዓ.ም የቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤና ትምህርት ፖሊሲ ማዕቀፍን አሻሽሎ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በቀዳማይ ልጅነት ፖሊሲ ትግበራ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።
በተለይም በገጠር አካባቢዎች የሚተገበረው የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ፕሮግራም የትምህርት ተደራሽነትን በ2003 ዓ.ም ከነበረበት 5.3 በመቶ በ2014 ዓ.ም ወደ 44 በመቶ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
በአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ "የአዲስ አበባ ተስፋዎች" በሚል የተጀመረው ፕሮግራም ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሕፃናትን እና 330 ሺህ ቤተሰቦችን በመድረስ ላይ ይገኛል።
በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት የሕፃናት የትምህርት ዝግጁነት መመዘኛ ውጤት በ2013 ዓ.ም ከነበረበት 68 በመቶ በ2017 ዓ.ም ወደ 84 በመቶ አድጓል።
በጤናው ዘርፍም "ቢግ ካች-አፕ" በተሰኘው ዘመቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ክትባት ያልወሰዱ ሕፃናትን መድረስ ተችሏል።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያ የቀዳማይ ልጅነት ፖሊሲ ቀርፃና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን ነድፋ ወደ ሥራ ብትገባም፣ አሁንም 40 በመቶ የሚሆነው የሕፃናት መቀንጨር መጠንና የሀብት እጥረት እንደ ትልቅ ፈተና ይነሳሉ።
ይሁን እንጂ በዘርፉ የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች ሀገራችን በ2022 ዓ.ም ሁሉም ሕፃናት በተሟላ የዕድገት ደረጃ ላይ እንዲገኙ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት ተስፋ ሰጪ መሠረት ጥለዋል።
በቀዳማይ ልጅነት ላይ የሚደረግ ማንኛውም ኢንቨስትመንት የዛሬ ሕፃናትን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ፣ ብቁና ምርታማ ትውልድ በመፍጠር የኢትዮጵያን የነገ ብሩህ ተስፋ የሚያረጋግጥ ነው።
በለሚ ታደሰ
#Ethiopia #EBC #EarlyChildhoodDevelopment #Education #FutureGeneration